ከሸገር እስከ ትውልድ - አቧራን አራግፎ የኢትዮጵያን መልክ የማሳየት ጉዞ

1 Day Ago 527
ከሸገር እስከ ትውልድ - አቧራን አራግፎ የኢትዮጵያን መልክ የማሳየት ጉዞ

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ሀብቶች የታደለች ምድረ ቀደምት ነች፡፡ እነዚህ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ሀብቶቿ ግን አቧራ ለብሰው በመኖራቸው ሳትጠቀምባቸው ኖራለች፡፡ "ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ" የሚባለው ቱሪዝም ለአንድ ሀገር ሁለት ጠቀሜታዎች ያሉት ነው፤ የመጀመሪያው የሀገር ገጽታን ማሳመር ሲሆን ሁለተኛው ገቢ ማስገኘት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዚህ የሚሆን የታደለች ምድር ብትሆንም የሚገባውን ያክል ሳትጠቀምበት ኖራለች፡፡

​ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መሪነት ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፏን ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ አካል አድርጋ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብታለች። እነዚህ ጥረቶች የሚያተኩሩት የቱሪዝም መሰረተ ልማትን በማጎልበት፣ የተፈጥሮ እና ባህላዊ መስህቦችን በማጉላት እንዲሁም ዘላቂ የቱሪዝም ተግባራትን በማስፋፋት ላይ ነው።​ እስቲ ጥቂት ወደኋላ ተጉዘን ዘርፉን እና የኢትዮጵያ መልክ የተገለጠበትን ፕሮጀክት እንቃኘው።

ገበታ ለሸገር

ገበታ ለሸገር አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ እንቁ ሀብቶችን አቧራ በማራገፍ ገጽታን ለማልማት ታልሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2011 ዓ.ም የተጀመረ ፕሮጀክት ነበር፡፡ በፐሮጀክቱም ከቤተ መንግሥት እስከ እንጦጦ ያሉ ውብ ሀብቶቻችን ለምተው የአዲስ አበባን ገጽታ ቀይረዋል፡፡ አንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ እና የመስቀል አደባባይ እድሳቶች የዚህ ፕሮጅት ውጤቶች ናቸው፡፡

የኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት እድሳት፣ የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሲጨመርበት ደግሞ አዲስ አበባን እውነተኛ ውበት ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ከነዚህ የቱሪዝም መዳረሻዎች ጋር ሲተሳሰር የእንግዶችን ቆይታ በመጨመር ረገድ የሚያደርገው አስተዋጽኦ በጣም ትልቅ ነው፡፡

ገበታ ለሀገር

ሐምሌ 2012 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጀመረው የገበታ ለሀገር መርሐ ግብር በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዋና ዋና የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ለማልማትና ለማሻሻል ያለመ ነበር። ሥራውም በጥራት እና በስኬት ተጠናቅቆ ተጨማሪ የኢትዮጵያ ውበቶችን አጉልቷል፡፡ ከነዚህ ፕሮጀክቶች መካከልም፡-  

ጎርጎራ ፕሮጀክት የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በአስደናቂ ሁኔታ ተሠርቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመረቀ ሲሆን፣ በፕሮጀክቱ የጎርጎራን ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ውበት ማጉላት ተችሏል፡፡ ቦታውም ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ይዘቱን ጠብቆ በዓለም አቀፍ ደረጃውን  ይዞ የለማ መዳረሻ ለመሆን በቅቷል። ​

ወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት በእሳተ ገሞራ የተፈጠረው የወንጪ ሀቅ የተፈጥሮ ውበት ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ይዘት ያለው ነው፡፡ ወንጪ ቂርቆስ ገዳም በዚሁ ሀይቅ ላይ የሚገኝ ጥንታዊ ገዳም ነው፡፡ ወንጪ የአካባቢ ጥበቃ እና የማኅበረሰብ ተሳትፎን ያጎላ ሌላው የገበታ ለሀገር ትሩፋት ነው። ​

የኮይሻ ፕሮጀክት ይህ በደቡብ የሀገራችን ክልል በሚገኘው የኮይሻ የተፈጥሮ ስጦታ ላይ የተሠራ ፕሮጀክት ነው፡፡ ሃላላ ኬላ እና ጨበራ ጩርጩራ የዚህ ፕሮጀክት አካላት ናቸው፡፡ በዚህም የአካባቢውን የተፈጥሮ ውበት እና ባህላዊ ቅርሶች ንዋያት ጎልተው እንዲወጡ ያደረገው ገበታ ለሀገር ነው። 

እነዚህ ፕሮጀክቶች ለዘላቂ ለአካባቢ ጥበቃ ቅድሚያ በመስጠት የአካባቢውን ማኅበረሰብ የህይወት ደረጃን ለማሻሻል፣ ቱሪዝምን ለማሳደግ እና የሥራ እድልን ለመፍጠር ያስቻሉ ናቸው። በዘላቂነት ደግሞ የኢትዮጵያን ገጽታ በመቀየር ከቱሪዝም ዘርፍ ሊገኝ የሚገባውን ጥቅም የሚያስገኙ ናቸው፡፡

ገበታ ለትውልድ

ገበታ ለሸገር እና ገበታ ለሀገርን በስኬት ያጠናቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለቀጣይ ትውልድ ስጦታ ገበታ ለትውልድን አስጀምረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገበታ ለሀገርን አጠናቅቀው ገበታ ለትወልድን ይፋ ሲያደርጉ የፕሮጀክቱ አንድ አካል የሆነውን የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርትን የመሠረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት፣ “‘ገበታ ለሸገር’ እና ‘ገበታ ለሀገር’ የቱሪዝም ሴክተር ልማት ሥራዎች በአብዛኛው ተጠናቅቀዋል። ይሄን ተከትሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ 8 የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማልማት የ‘ገበታ ለትውልድ’ ሐሳባችንን ገፍተንበታል። የዐርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርትን በ120 ሄክታር መሬት ላይ፣ የአባያ ሐይቅን እያየ በሚያማምር ቦታ ላይ እንዲገነባ ዛሬ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠናል።”

“በዓመት ከመንፈቅ ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቀው ይህ ፕሮጀክት 1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ዶላር የሚሸፍነውን ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ዘርፍ ገቢን ተቋዳሽ እንድንሆን ያደርገናል። ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ሀብታችንን በመጠቀም ሀብት የማፍራት ጅምሮችን በማስፋፋት፣ የብልጽግና ጉዟችንን ለማሳካት እንተጋለን” ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኒሼቲቭ የሆነው ገበታ ለትወልድ ስምንት የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን በማልማት የሀገሪቱን የቱሪዝም መሰረተ ልማት ለማጎልበት እና ዘላቂ ልማትን ለማስፋፋት ዓላማ አድርጎ የተነሳ ነው። እነዚህ ፕሮጀክቶች በትግራይ፣ በሶማሊ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ እንዲሁም በአማራ ክልል የሚሠሩ ሲሆኑ፣ ቦታዎቻቸውም ተለይተው ወደ ተግባር ተገብቷል።

የኢትዮጵያን የተፈጥሯዊ፣ ሰው ሠራሽ እና ባህላዊ ቅርሶችን በማልማት ቱሪዝም ለሀገር ገጽታ ግንባት እና ኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የሚረዱም ናቸው፡፡ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ሀገሪቱን ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግም ከዓላማቸው መካከል ናቸው። ​

ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ቱሪዝም ከግብርና፣ ከማምረቻ፣ ከማዕድን እና ከመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች (ICTs) ጎን ለጎን ከኢትዮጵያ አምስት ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ሆኗል፡፡ ይህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መንግሥት የቱሪዝም ልማትን በሀገሪቱ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ውስጥ የማካተት አካል ነው። ይህ ስትራቴጂያዊ ትኩረት መንግሥት ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ቱሪዝምን ለመጠቀም ያለውን ቁርጠኝነት ያጎላ ሆኗል። ​

የቱሪዝም መሰረተ ልማት ግንባታዎቹ በስኬት የተጠናቀቁ እና እየተጠናቀቁ ያሉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን እያስቻሏት ናቸው፡፡ ይህ ስከኬትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢጋድ "የቱሪዝም ሻምፒዮን" ተብለው እንዲሰየሙ አስችሏቸዋል። ከዚያም አልፎ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያመጣችው ለውጥ በአፍሪካ ግንባር ቀደም መሆኗ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመስክሮለታል። እነዚህ ዕውቅናዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቱሪዝም ዘርፉን ከፍ ለማድረግ ያሳዩትን ተነሳሽነት እና ውጤታማነታቸውን አጉልተው ያሳዩ ናቸው። ​

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top