ስመ ጥሩ እንግሊዛዊ ሳይንቲስት ስቴቨን ሃውኪንግ እ.አ.አ በ1995 ዓለም ከ30 ዓመታት በኋላ ምን ልትመስል ትችላለች የሚል ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፡፡
የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2025 ዛሬ መግባቱን አስመልክቶ የፊዚክስ ሊቁን ትንበያዎች ከ30 ዓመት በኃላ በምልሰት እንቃኛቸዋለን፡፡
የቲዎሬቲካል ፊዚክስ ሊቁ በ30 ዓመታት ውስጥ የሚጠበቁ ግዙፍ ለውጦች ብሎ ካነሳቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በየዘርፉ የቴክኖሎጂው መፍላት ነው፡፡ ሃውኪንግ የበይነ መረብ ጥቃት፣ የኮምፒዩተር ቫይረስ እና የመረጃ ምንተፋዎች እንደሚስፋፉ የተናገራቸው ትንበያዎች ባለ ጥቁር ምላስ ሊያስብሉት ይችላሉ፡፡
ሌላኛው ኢንተርኔትን መሰረት ያደረገ የርቀት ህክምና አገልግሎት ትንበያው ሲሆን ሊቁ ስልጡን ሮቦት ሀኪሞችን የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ብሎ ነበር፡፡ ይህ የሃውኪንግ ትንበያ ሙሉ በሙሉ ባይሳካም በተለያዩ የዓለም ሀገራት ጅማሮዎች ግን ተስተውለዋል፡፡
የሰው ልጅ ከህዋ ላይ ውድ ማዕድናትን ወደ ምድር ማጋዝ እንደሚጀምር በፊዚክስ ሊቁ የተሰጠው ትንበያ፤ ናሳን ጨምሮ የተለያዩ የጠፈር ምርምር ማዕከላት ከጨረቃ መጡ የተባሉ ድንጋዮችን በሙዚየም እስከማሳየት ቢደርሱም እስከ ማዕድን ቁፋሮ ስለመድረሳቸው ግን መረጃ ማግኘት አይቻልም፡፡
በህዋ ላይ ማዕድናት ያማውጣት ስራ ባይጀመርም፤ እድሉ ግን አሁንም እንዳለና በህዋ ላይ ያሉ ሰው ሰራሽ ቁሳቁሶች ለጠፈርተኞች እንቅስቃሴ እክል መሆናቸው ይገለጻል፡፡
ሳይንቲስቱ በትንበያው ከ30 ዓመታት በፊት ሊከሰት ይችላል በሚል ያቀረበው ሌላኛው ጉዳይ በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ገንዘብ ከባንክ መክፈያ ማሽን ማውጣት የሚቻልበት ቴክኖሎጂ በወደፊቱ የባንክ ዘርፍ ተግባራዊ ይሆናል የሚል ነበር፡፡
የሳይንቲስቱ ግምቶች እውን ሆነው ዲጂታል የባንክ አገልግሎት መስጠት፤ በጣት አሻራ እንዲሁም ስካን በማድረግ ደንበኞች ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ የሚችሉበት ዘመን እውን ሆኗል፡፡
ቢቢሲ በዓለም አቀፍ ፕሮግራሙ ሳይንቲስቱ ስቴቨን ሃውኪንግ ያስቀመጣቸው ትንበያዎች በርካቶቹ እውን መሆናቸውን ቢገልጽም፤ የትላልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋትን መዘንጋቱን አስታውሷል፡፡
በላሉ ኢታላ