ከ7 ዓመታት በፊት የተደረገው ሀገራዊ ለውጥ ከመንግስት ብቻ የነበረውን የተግባቦት ፍሰት በመቀየር ህዝብን ያሳተፈ፣ ተገቢ እና ወቅታዊ መረጃ ለማህበረሰቡ የሚሰጥ የኮሙኒኬሽን ሥርዓት እንዲገነባ ማድረጉን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ለውጡ ኢትዮጵያ ከነበራት ኋላ ቀር የፖለቲካ ባሕል ተላቃ በሃሳብ የተመሰረተ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲኖራት ያስቻለ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የሚዲያ ብሎም የተቋማትን ነፃነት ማረጋገጥ በለውጡ መንግስት ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ፣ ሽግግሩ የፖለቲካ ምህዳሩን ያሰፋ እና በርካታ ማሻሻያዎችን ያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም አሳሪ የነበሩ የሚዲያ፣ የፀረ-ሽብር እና የሲቪል ማህበረሰብ ሕጎችን በማጤን ማሻሻል መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የለውጡ መንግስት የራሱ የኮሙኒኬሽን ተቋም እንዳልነበረው በማስታወስ፣ በጋራ ትርክት እና ግብ ላይ የሚያተኩር ሀገረ መንግስት ማቋቋም ለሚለው እሳቤ የተሰለፈ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል የኮሙኒኬሽን ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡
በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ የመንግስትን አቋም ማመላከት፣ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማሳወቅ እና ሌሎችም ብቃት ያላቸውን መረጃዎች ለማህበረሰቡ ማድረስ የተቋሙ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ተቋሙ ለፖለቲካ ሥርዓት መረጋጋት፣ ለሰላም መስፈን፣ ለሀገር አንድነት እና የተዛቡ መረጃዎችን ለማጥራ አበክሮ እየሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል፡፡