የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙቴ ኤጌዴ "ግሪንላንድ አትሸጥም" ሲሉ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምላሽ ሰጥተዋል።
ትናንት በዋሽንግተን በተካሄደው የጋራ ኮንግረስ ስብሰባ ላይ ዶናልድ ትራምፕ ባደረጉት ንግግር፣ ግሪንላንድን “በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ” የአሜሪካ አካል እንደሚያደርጓት ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙቴ ኤጌዴ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው "ግሪንላንድ የኛ ናት፤አትሸጥም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
"ግሪንላንድ የግሪንላንድ ነዋሪዎች ብቻ ናት" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዶናልድ ትራምፕ ደሴቲቱን የመግዛት አወዛጋቢ ፍላጎት ምኞት ብቻ ሆኖ እንደሚቀር ነው የገለጹት።
"እኛ አሜሪካውያን አልያም ዴንማርካዊ አይደለንም፤ ለሽያጭ የቀረብን እና በቀላሉ ልንወሰድ የምንችልም አይደለንም" ሲሉ ነው የግሪን ላንድ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በነዋሪዎቿ መሆኑን በመልዕክታቸው ያስገነዘቡት።
ዶናልድ ትራምፕ በትናንትናው ንግግራቸው "የራሳችሁን የወደፊት እድል የመወሰን መብታችሁን እናከብራለን፤ እኛን ከመረጣችሁ ወደ አሜሪካ እንቀበላችኋለን" ሲሉ ለግሪንላንድ ነዋሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
አክለውም ግሪንላንድን ደህንነቷን በመጠበቅ እና በማበልጸግ ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ ከፍታ ላይ አብረን እናደርሳታለን ሲሉ ተናግረዋል።
ስልጣን ከያዙ ማግስት ጀምሮ በግሪንላንድን ላይ ያላቸውን ፍላጎት ሲገልጹ የቆዩት ትራምፕ፤ ደሴቲቷን በመያዝ የአሜሪካን ብሔራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ደህንነት እንደሚያሻሽሉ መናገራቸውን ኤቢሲ ኒውስ ዘግቧል።
በአርክቲክ እና በአትላንቲክ ውቅያኖሶች መካከል የምትገኘው የዓለማችን ትልቋ ደሴት ግሪንላንድ ከ1979 ጀምሮ የዴንማርክ ራስ ገዝ ግዛት አካል ነች።