የካቶሊክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሮም ኤጲስ ቆጶስ ተብለውም ይጠራሉ፡፡ በመንፈሳዊም ሆነ በአስተዳደራዊ ሁኔታ የመላው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ እና የበላይ ጠባቂ ናቸው፡፡ ይህም ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ሲሸጋገር የመጣ ነው። አባትነታቸው እና ሥልጣናቸው ከ1.3 ቢሊዮን በላይ ለሚሆኑ በመላው ዓለም ለሚገኙ ካቶሊኮች ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም በዲፕሎማሲ፣ በሥነ ምግባር አመራር እና በሃይማኖች መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል።
በመላው ዓለም ያለው የካቶሊክ ምዕመን በአንድ ማዕከላዊ አስተዳደር የሚመራ ነው፡፡ ቤተ-ክርስቲያኒቷ ይህን ማስቀጠል የቻለችው ባለት ጥብቅ ዲሲፕሊን እና በነጻነት መወሰን በመቻሏ ነው፡፡ ቫቲካን በዓለም ላይ ዕውቅናን ያገኘች ትንሽ ሀገር ብትሆንም ተፅዕኖዋ ግን በመላው ዓለም ላይ የሚገለጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የጣሊያን መንግሥትም ሆነ ማንኛውም ዓለማዊ አስተዳደር በውሳኔዋ ስለማይገባ ነው፡፡ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጥብቅ ዲሲፕሊን ከምትከውናቸው ሥርዓቶች መካከል የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫዋን ቀጥለን እንመለከታለን፡፡
የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሚመረጡበት ሚስጥራዊ ሂደት "ኮንክሌቭ" ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ታሪክ አለው። ይህ ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ያላት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ተተኪ ምርጫ ሚስጢራዊ እና ተዓማኒ እንዲሆን አስችሎ የቀጠለ ነው።
በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሚመረጡት በሮም ቀሳውስት እና ምዕመናን ሲሆን፣ ይህም የነገሥታቱ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ቤተሰቦች ጫና እንዲያርፍበት አድርጎት ነበር። ሂደቱም ሥርዓት አልበኝነትን የሚያሰፋ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ያጋለጣት እንደነበር ታወቀ።
እ.አ.አ በ1059 የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዳግማዊ ኒኮላስ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ምርጫ በካርዲናሎች ውሳኔ ብቻ እንዲሆን ደነገጉ። ዳግማዊ ሊኮላስ ይህንን የወሰኑት ዓለማዊ ተጽዕኖዎችን እና ውስጣዊ መከፋፈልን ለማስቀረት ነበር። ያም ሆኖ ግን ሂደቱ አሁን ያለውን ቅርፅ እስከሚይዝበት ጊዜ ድረስ ውጫዊ ተፅዕኖው ቀጥሎ ነበር፡፡
አሁን ያለውን የምርጫ ሥርዓት የሠሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ግሪጎሪ 10ኛ ናቸው። ይህም የሆነበት ምክንያት ከዚያ በፊት ምርጫውን ለማካሄድ እስከ ሦስት ዓመታት ይዘገይ ስለነበር ነው፡፡ የመዘግየቱ ምክንያቶችም ካርዲናሎቹ ከሚመጡበት አካባቢ ጋር በተያያዘ ስለሚከፋፈሉ፣ የነገሥታቱ እና ባለሥልጣናት ተፅዕኖ እና ለምርጫውም ግልፅ ሕግ እና መመሪያ ስላልነበረ ነው፡፡
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ክሌመንት አራተኛ በ1268 ካረፉ በኋላ ካርዲናሎች ተተኪያቸውን ግሪጎሪ 10ኛን ለመምረጥ 3 ዓመት ገደማ ፈጅቶባቸው ነበር። ቪተርቦ በተባለችው የጣሊያን ግዛት ሲካሄድ በነበረው በዚያ ምርጫ ካለመጠን መጓተት የተበሳጩት የአካባቢው ነዋሪዎች ካርዲናሎች ላይ ቤቱን ቆልፈው ውሳኔውን በፍጥነት እንዲያሳውቁ አስገደዱአቸው። ካርዲናሎቹ ተዘግቶባቸውም መዘግየታቸውን የተረዱት ነዋሪዎቹ ጣሪያውን አፈረሱባቸው፡፡ ተዘግቶባቸ በምግብም እጥረት እና በፈረሰው ጣሪያ ምክንያት ብርድ ያንገፈገፋቸው ካርዲናሎችም ፖፕ ግሪጎሪ 10ኛን መርጠው ሂደቱን አጠናቀቁ፡፡
ፖፕ ግሪጎሪ 10ኛ በእርሳቸው ምርጫ ወቅት የተከሰተውን ችግር ለማስቀረትም በ1274 ‘ኮንክሌቭ’ የተሰኘውን ሥርዓት ደነገጉ፡፡ ይህም ዘመናዊው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ምርጫ ሥርዓት በይፋ መጀመር መነሻ ሆነ። ፖፕ ግሪጎሪ 10ኛ ከሥርዓቱ ጋርም ካርዲናሎቹ ከሕዝብ ጋር እንዳይገናኙ፣ የተመጠነ የምግብ እና የኮሙኑኬሽን አገልግሎት ብቻ እንዲኖር እና ሁለት ሦስተኛው ጉባኤ የመረጠው ካርዲናል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሆን ሥርዓት ሠሩ፡፡
በምርጫው የሚሳተፉት ካርዲናሎች ዕድሜያቸው ከ80 ዓመት በታች መሆን አለበት፡፡ የሚሰበሰቡበት ቦታ ሲስታይን ቤተ ክርስቲያን፣ ቫቲካን ውስጥ ነው፡፡ መራጮቹ ማንኛውንም ሚስጢር ላያወጡ ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ፣ ይህን ቃላቸውንም እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ይጠብቁታል፡፡ በዚህም ምክንያት ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ምርጫ ላይ ምንም ዓይነት ውዝግብ እና ሃሜት ሲነሳ አይታይም፡፡
ምርጫው ከመጀመሩ በፊት ካርዲናሎቹ በቤተ-ክርስቲያን ተሰብስበው በጋራ ይፀልያሉ፡፡ ከሕብረት ፀሎቱ በኋላ የድምፅ መስጠት መርሐ ግብሩ ይጀመራል፡፡ ምርጫው በየቀኑ ጧት ሁለት ጊዜ እና ከሰዓት ሁለት ጊዜ በአጠቃላይ አራት ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፣ መራጮቹ እንዲመረጥ ያሰቡትን ሰው ስም ጽፈው በተዘጋጀው ድምጽ መስጫ ውስጥ ያስቀምጣሉ፡፡ ይህ ከተከናወነ በኋላ በምርጫው ሁለት ሦስተኛ ድምጽ ያገኘ ካርዲናል ከሌለ ውጤቱን በጉጉት ለሚጠብቀው ሕዝብ አለመሳካቱን ለማሳወቅ ጥቁር ጭስ ይለቀቃል፡፡ ይህ ሂደትም የሚፈለገው ድምጽ እስከሚገኝ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
የሚፈለገው ሁለት ሦስተኛ ድምጽ ሲገኝ ደግሞ ምርጫው መሳካቱን ለምዕመናኑ ለማስታወቅ ነጭ ጭስ ይለቀቃል፡፡ ጥቁሩን ጭስ ለማውጣት የፖታሲየም ፐርክሎሬት (KClO₄)፣ አንትራሰን (መዓዛ ያለው ሃይድሮካርቦን) እና ድኝ(ሰልፈር) ውህድን ይጠቀማሉ፡፡ ነጩን ጭስ ለማውጣት ደገሞ ፖታሲየም ክሎሬት (KClO₃)፣ ላክቶስ እና ሮሲን የተባሉ ኬሚካሎችን ውህድ ይጠቀማሉ፡፡
የተመረጡት ካርዲናልም መመረጣቸውን እንደሚቀበሉ ይጠየቃሉ፡፡ መመረጣቸውን ሲቀበሉም የካርዲናሎቹ ሰብሳቢ በመጨረሻም መሪ አገኘን በማለት ምርጫውን ይፋ ያደርጋሉ፡፡ የተመረጡት ፖፕም በቀይ መጋረጃ በተዘጋጀ ሰገነት በኩል ወጥተው ንግግር ያደርጋሉ፡፡ በንግግራቸውም በቤተክርስቲያኒቱ ሊሠሩአቸው ስለሚያስቡአቸው ነገሮች፣ ለዓለም ሰላም ያላቸውን ሀሳብ እና ለሰው ልጆች ደህንነት መሠራት ስላለባቸው ጉዳዮችን ያካትታሉ፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከአዲሱ ጳጳስ ምርጫ የማስጀመሪያ ስርዓተ ቅዳሴ ጀምሮ እስከ ምርጫ መጠናቀቁን የሚያበስረው የነጭ ጭስ መርኃ ግብር ድረስ የቫቲካን ሚዲያ የኮንክሌቭ ቀጥታ ስርጭትን በቪዲዮ እና በድምጽ ለማስተላለፍ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ቫቲካን ኒውስ ባወጣው መረጃ መሰረት 267ኛውን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ስነ ስርዓትን በቴሌቪዠን፣ በሬዲዮ እና በማህበራዊ ሚዲያዎች በተለያዩ ቋንቋዎች መከታተል እንደሚቻል ተገልጿል።
በለሚ ታደሰ