ትኩሳት የማያጣው የኢራን እና አሜሪካ ጨዋታ በትልቁ መድረክ

2 Days Ago 3463
ትኩሳት የማያጣው የኢራን እና አሜሪካ ጨዋታ በትልቁ መድረክ
በ1979 የአሜሪካ ሁነኛ ሰው የነበሩት ረዛ ሻህን ከስልጣን ካስወገደው የኢራን አብዮት በኋላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የሻከረበት ነው። ከዚህ ጊዜ በኋላ ባለፉት 45 ዓመታት የሀገራቱን ግንኙነት መስመር ለማስያዝ ሀገራት የተለያዩ የዲፕሎማሲ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ለውጥ አልመጣም።
 
ከኢራን አብዮት19 ዓመት በኋላ ግን ሀገራቱ በአንድ መድረክ የተፋጠጡበት አጋጣሚ ተፈጠረ። 1998 ፈረንሳይ ዓለም ዋንጫ።
 
በዚህ ትልቅ የእግር ኳስ ድግስ ሀገራቱ በአንድ ምድብ ተደልድለዋል። የዓለም መገናኛ ብዙሀን ትኩረትም አይንህን ለአፍር የሚባባሉት አሜሪካ እና ኢራን እንዴት በአንድ ሰላማዊ ትግል ለዚያውም እርስ በእርስ ይገናኛሉ የሚለው ሆነ።
 
ጀርመን እና ዩጎዝላቪያ ባሉበት ምድብ 6 የተደለደሉት ባላንጣዎቹ የሚገናኙበት ጊዜ ደርሶ ወደ ሜዳ ከመግባታቸው በፊት ስጋት የነበረበት የዓለም እግር ኳስ የበላይ ጠባቂ ፊፋ የጥንቃቄ ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል።
 
በወቅቱ በቀድሞው የኢራቅ መሪ ሳዳም ሁሴን የሚደገፍ ሙጃሂዲን ሀልክ በተባለ አማጺ የሚመራ ቡድን የኢራንን ስም ለማጠልሸት እና በስቴዲየም ተቃውሞ ለማስነሳት 7 ሺህ ትኬቶች ገዝቶ አሰማርቶ እንደነበር ፎር ፎር ቱ የተባለ ጋዜጣ ሰፊ ሀተታ ባወጣበት ጽሁፉ ላይ አስፍሮ ነበር።
 
መረጃው ደርሶት የነበረው የፈረንሳይ ፖሊስም ተጨማሪ ሃይል በመመደብ ከእግር ኳስ ባለፈ የፖለቲካ ትኩሳት ያለበትን ጨዋታ መጠባበቅ ይጀምራል።
 
ዓለም ላይ ያለ የእግር ኳስ አፍቃሪ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካውን የሚከታተል ሁሉ የአሜሪካ እና ኢራንን ጨዋታ በጉጉት ይጠብቃል።
የሁለቱ ቡድን ተጫዋቾች በሲውዘርላንዳዊው ዋና ዳኛ ኡርስ ሜር መሪነት ወደ ሜዳ ገቡ።
 
ግን በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭትም ይሁን በስቴዲየም ተገኝቶ የሚከታተለው ደጋፊ ሁሉም ነገር እንደፈራውም እንደጠበቀውም ሳይሆን ቀረ።
 
ኢራናውያን ተጫዋቾች ነጭ አበባ ይዘው ለአሜሪካውያኑ ሰጧቸው። ይህን ያልጠቁት እና ከተጋጣሚያቸው የሰላም እጅ የተዘረጋላቸው አሜሪካውያኑ በደስታ አቀፏቸው በጋራም የማስታሻ ፎቶ ተነሱ።
 
በሊዮን የተደረገው ጨዋታም በኢራን 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቀቀ። ዓለምን አንድ የማድረግ ሀይል ያለው ስፖርት ለ19 ዓመታት የሻከሩትን ሀገራት በሰላም አጨባበጣቸው።
 
የሚገርመው ከ18 ወራት በኋላም የኢራን ብሄራዊ ቡድን ወደ አሜሪካ ተጉዞ በካሊፎርኒያ የወዳጅነት ጨዋታ አድርጓል።
 
ፖለቲከኞቹ ለ20 አመታት በሀገራቱ መካከል ያለውን ውጥረት ማርገብ የተሳናቸውን ጉዳይ እግር ኳስ በ90 ደቂቃ መፍትሄ አበጅቶለት ነበር ምንም እንኳን ዘላቂነት ባይኖረውም።
 
በዚያ ሁነት የሁለቱም ሀገራት ደጋፊዎች በደስታ በጋራ የቆሙበት እና ፊፋ ለሁለቱም ቡድኖች የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት የሰጠበት ሆኖ አልፏል።
 
2026 ዓለም ዋንጫ ደግሞ ሌላ ትኩሳት። ኢራን ወደ አሜሪካ
 
አሜሪካ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጣምራ በሚያዘጋጁት የዓለም ዋንጫ ኢራን ቀደም ብላ ማለፏን አረጋግጣለች። ከኢራን ማለፍ በኋላ በርካታ ጉዳዮች እየተነሱ ይገኛሉ።
 
ዶናልድ ትራምፕ እና መንግስታቸው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ክልከላ ከጣሉባቸው የመጀመርያ 10 ሀገራት አንዷ ኢራን መሆኗ ከወዲሁ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።
 
ምንም እንኳን በዓለም ዋንጫው ከሚሳተፉት ሀገራት ብዛት አንጻር ኢራን እና አሜሪካ በምድብ ጨዋታ የሚገናኙበት ዕድል ጠባብ ቢሆንም ፊፋ ከወዲሁ ከአሜሪካ መንግስት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ይፋ ተደርጓል።
 
ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው የአሜሪካ የኢሚግሬሽን ጉዳዮች አስተዳደር ለዓለም ዋንጫው የሚጓዙ ደጋፊዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ሌሎችንም በተመለከተ ጠበቅ ያለ ማጣራት እንደሚያደርግ ይፋ መሆኑ የኢራንን የመሳተፍ ህልውና ጥያቄ ውስጥ ሊከተው ይችላል ተብሏል።
 
በአንተነህ ሲሳይ
 
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top