ከትንሿ ቶሎሳ እስከ ግዙፉ የዓለማችን ክለብ የዘለቀው የዣቢ አሎንሶ ስኬት

6 Days Ago 679
ከትንሿ ቶሎሳ እስከ ግዙፉ የዓለማችን ክለብ የዘለቀው የዣቢ አሎንሶ ስኬት

ቶሎሳ በሰሜናዊ ስፔን ባስክ ግዛት የምትገኝ ትንሽዬ፣ ግን ታሪካዊት ከተማ ነች። ስፋቷ 37.93 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ 18 ሺህ 96 ነዋሪዎች አሏት።

የዛሬው ባለ ታሪካችን ዣቢ አሎንሶ እ.አ.አ ኖቬምበር 25 ቀን 1981 የተወለደው በዚህችው ከተማ ነው።

ከዚህች ትንሽ ከተማ የጀመረው የእግር ኳስ ሕይወቱ አሁን ለታላቁ ሪያል ማድሪድ አሠልጣኝነት ደርሷል።

የአሎንሶ የተጫዋችነት ጊዜ በዓይነቱ ልዩ በሆነ የቦታ አያያዝ፣ ኳስን የማቀበል ብቃት፣ በታክቲክ ብልጠት እና መሐል ሜዳን በማረጋጋት ይገለጻል። 

በ10 ዓመቱ ኳስ መጫወት የጀመረው ከአሁኑ የአርሰናል አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ጋር አንቲጉኮ በተባለ ክለብ ሲሆን፣ በ12 ዓመቱ ወደ ሪያል ሶሲዳድ በመዛወር የቀጣይ የእግር ኳስ ሕይወቱን ወሳኝ ምዕራፍ ጀመረ። 

እ.አ.አ በ2004 ሊቨርፑልን ተቀላቅሎ አምስት ዓመታትን ከክለቡ ጋር በመቆየት የ2005ቱን የማይረሳ የአውሮፓ ሻምፒዮምስ ሊግን፣ የአውሮፓ ሱፐር ካፕን አና የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕን አንሥቷል።

ከሊቨርፑል ቀጥሎ ሪያል ማድሪድን የተቀላቀለው አሎንሶ፣ በዚያ አምስት ስኬታማ ዓመታትን አሳልፏል።

የሪያል ማድሪድ ቆይታው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚጠሩት የአማካይ ስፍራ ተጨዋቾች ተርታ እንዲመደብ አስችሎታል። 236 ጨዋታዎችን በማድረግም ስድስት ዋንጫዎችን አሸንፏል።

ከእነዚህም መካከል የ2014 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ (ላ ዴሲማ)፣ አንድ የላሊጋ ዋንጫ፣ ሁለት የኮፓ ዴላ ሬይ ዋንጫዎች እና አንድ የስፔን ሱፐር ካፕ ዋንጫዎች ይገኙበታል። 

በጀርመኑ ባየር ሙኒክ ሦስት ዓመታት ቆይታውም ሦስት የጀርመን ቡንደስ ሊጋ፣ አንድ የጀርመን ዋንጫ እና አንድ የጀርመን ሱፐር ካፕን በማሸነፍ ታሪኩን በወርቅ ቀለም ጽፏል። 

ከክለብ ስኬቱም በተጨማሪ ከብሔራዊ ቡድን ጋርም በ2010 የዓለም ዋንጫን፣ በ2008 እና በ2012 የአውሮፓ ዋንጫዎችን ያሸነፈው የስፔን ወርቃማ ትውልድ ወሳኝ ተጫዋችም ነበር።

የአሠልጣኝነት ሥራውን የጀመረው አንድ ዓመት በቆየበት የሪያል ማድሪድ አካዳሚ ሲሆን፣ ከ14 ዓመት በታች ቡድኑን የዋንጫ ባለቤት በማድረግ ወደ ሊግ ውድድር ደረጃ አሳድጎታል።

በ2019 ወደ ሪያል ሶሲዳድ ሁለተኛ ቡድን በመዛወር ቡድኑን በ2021 ወደ ስፓኒሽ ሴጉንዳ ዲቪዥን አሳድጎታል። በዚህ ሥራው የወጣቶችን ተሰጥኦ የመለየት እና መጠቀም ብቃቱን አስመስክሮበታል።

በ2022 ዋና አሠልጣኝነት በተቀላቀለው ባየር ሌቨርኩሰን ልዩ የአሠልጣኝነት ብቃቱን አስመስክሯል።

በጥቅምት 2022 ሥራውን ሲጀምር ቡድኑ በወራጅ ቀጠና ሲዳክር የነበረ ሲሆን፣ በመጀመሪያ ዓመቱ ከወራጅ ቀጣና አውጥቶ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ከማጠናቀቁም በላይ ቡድኑን ለየትኛውም ክለብ ምሕረት የሌለው አስፈሪ አድርጎታል።

በ2023/2024 የውድድር ዘመን ሌቨርኩሰን የመጀመሪያውን የቡንደስ ሊጋ እና የጀርመን ዋንጫ አሸናፊ በማድረግ በክለቡ የታሪክ ማኅደር ስሙን ከቀዳሚዎቹ ተርታ አስመዝግቧል። 

አሎንሶ እንደ ፔፕ ጓርዲዮላ፣ ሆዜ ሞሪንሆ፣ ካርሎ አንቸሎቲ፣ ቪሴንቴ ዴልቦስኬ እና ራፋኤል ቤኒቴዝ ባሉ ታላላቅ አሠልጣኞች ሥር ተጫውቷል። ይህም ለአሠልጣኝነት ፍልስፍናው አስተዋፅኦ እንዳደረገለት ሆዜ ሞሪንሆ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በጨዋታ ወቅት በፈጣን እንቅስቃሴ፣ ቶሎ ቶሎ ቦታ በመቀያየር ተቃራኒ ቡድንን ፋታ የመንሳት ስልትን ይከተላል።

ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጭ ንቁ ሆኖ በመገኘት እና ፈጣን እንቅስቃሴን በማድረግ ተጋጣሚን ማዛባት ሌላው የጨዋታ ስልቱ ነው።

የእያንዳንዱን ተጫዋች ደረጃ በማሻሻል እና የጋራ መግባባት በመፍጠር ጠንካራ የቡድን መንፈስን መፍጠር ሌላው የስኬቱ ቁልፍ ምሥጢር ነው። 

በሥልጠናም ሆነ በጨዋታ ወቅት ለቡድኑ ግልጽ መመሪያዎችን እና ሐሳቦችን በመስጠት የሚሠራውን የሚያውቅ ቡድን መፍጠር ሌላው ልዩ መለያው ነው። 

አሎንሶ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሪያል ማድሪድ ዋና አሠልጣኝ የሚያደርገውን ስምምነት ተረራርሟል። ይህ ሥራ ራሱም በጥብቅ የሚፈልገው እና ወደ ቤቱ የተመለሰበት መሆኑ ይነገራል።

በሌቨርኩሰን ቤት የተቀዳጀው ስኬቱ እና ከሪያል ማድሪድ ጋር ያለውን ጠንካራ ትሥሥር ግምት ውስጥ በማስገባትም ነጮቹ የሚፈልጉትን ስኬት ወደ ቤርናባው ይመልሳል የሚል ሰፊ ግምት ተሰጥቶታል።

ሥራውን በይፋ የሚጀምረው እ.አ.አ ሰኔ 1 ቀን 2025 ሲሆን፣ የመጀመሪያው ትልቁ ፈተናው በክረምቱ የሚካሄደው የዓለም ክለቦች ዋንጫ ላይ ቡድኑን ወደ ስኬት መምራት ይሆናል። 

ከቀጣይ ዓመት ጀምሮም ሪያል ማድሪድን በሀገር ውስጥ ውድድሮች ስኬታማ ማድረግ ዋነኛው ኃላፊነቱ ነው።

በሌላ በኩል ክለቡ የያዘውን የአውሮፓ ንግሥና ማስቀጠል፣ እነዚህ ሁሉ ስኬቶችን ለማስቀጠልም ክለቡ አሁን እየሄደበት ያለውን ታዳጊዎችን ልምድ ካላቸው ጋር በማቀናጀት ተፅዕኖ ፈጣሪነቱን ማስቀጠል ይጠበቅበታል።

ከሁሉም በላይ ግን በዚህ ዓመት ያለዋንጫ በማጠናቀቅ የተከፋውን ደጋፊ ልብ መመለስ ዋናው ተልዕኮው ነው።

እሱም የክለቡ አሠልጣኝ መሆኑን ይፋ በተደረገበት ወቅት እንዳለው ደጋፊው "የኔ ሪያል ማድሪድ ይህ ነው" የሚልበትን የውብ ጨዋታ ባህል ለመፍጠር እንደመጣ ተናግሯል።

ተሳክቶለት የዚህ ዓመቱን የክለቡን የውጤት ማጣት ዐይነጥላ ይገፍፍ ይሆን?

በለሚ ታደሰ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top