ሩሲያ በልዩ ሁኔታ የምታከብረው የሁለተኛው ዓለም ጦርነት የድል ቀን

4 Hrs Ago 324
ሩሲያ በልዩ ሁኔታ የምታከብረው የሁለተኛው ዓለም ጦርነት የድል ቀን

ሩሲያ የሁለተኛ ዓለም ጦርነት የድል ዕለትን በየዓመቱ ሜይ 9 በሞስኮ የሚገኘው ቀዩ አደባባይ በደማቅ ወታደራዊ ትርዒት ታከብራለች፡፡ ይህ የሩሲያ አከባበር በዓለም ላይ ካሉት ሀገራት ሁሉ እጅጉን የላቀ ድምቀት ያለው ነው። ይህ ታላቅ ትዕይንት “ሶቪየት ኅብረት” በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት “በናዚ” ላይ ድል መቀዳጀቷን የሚያስታውስ እና ሩሲያውያን ልዩ የሀገር ፍቅራቸውን የሚገልጹበት ነው። ሰልፉ ከድሉ መታሰቢያነቱ ባሻገርም እንደ ብሔራዊ የመታሰቢያ ቀን የሚታይ ሲሆን፣ ሩሲያ የጦር ኃይሏን አቅም እንዲሁም ታሪካዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ትኩረቷ መግለጫ ሆኖም ያገለግላል።

“ናዚ” አውሮፓን በተቆጣጠረበት ወቅት እጅ ካልሰጡ ሀገራት መካከል ሩሲያውያን ይገኙበታል፡፡ የናዚ ጦር በመጀመሪያው ዙር ጦርነት የ”ሶቭየት ሕብረትን” ጦር አሸንፎ የነበረ ቢሆንም ሩሲያውያን ግን እንደገና ተደራጅተው 24 ሚሊዮን ዜጎቻቸውን ሰውተው አሸንፈዋል፡፡ ይህ የሩሲያ መስዋዕትነት ከ15 እስከ 17 ከሚሆነው የአውሮፓ ሀገራት መስዋዕትነት የላቀ ሲሆን፣ በጦርነቱ ምክንያት በመላው ዓለም ከተከፈለው የሰው ህይወት 40 በመቶውን እንደሚሸፍን የታሪክ ማስረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የመጀመሪያው የድል ሰልፍ በ”ሶቭየት ሕብረት” የተካሄደው “ናዚ” ከተሸነፈ ከአንድ ወር በኋላ እ.አ.አ ሰኔ 24 ቀን 1945 ነበር። በቀዩ አደባባይ በተካደው ሰልፍ ላይ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ስታሊን የተገኙ ሲሆን፣ ማርሻል ጆርጂ ጁኮፍ በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጠው ሰልፉን መርተዋል።

በዚህ የመጀመሪያ ሰለፍ ላይ ከ40 ሺህ በላይ የሶቭየት ወታደሮች ተገኝተዋል፡፡ በዕለቱ በምርኮ ከተያዙ ወታደሮች የናዚ አርማዎችን የመጣል ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል። ከሁሉም የሶቪየት ጦር ግንባር የተውጣጡ ወታደራዊ ክፍሎች እንዲሁም በጦርነቱ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ መሣሪያዎችም ለእይታ ቀርበውበታል።

ምንም እንኳ የመጀመሪያው ሰልፍ የተካሄደው በፈረንጆቹ ሰኔ ወር ቢሆንም ናዚ ለመጨረሻ ጊዜ እጁን የሰጠው እ.አ.አ ሜይ 8, 1945 በበርሊን ነው። ሶቭየት ሕብረት ሜይ 9 የድል ቀን አድርጋ የምታከብረው በሰዓት አቆጣጠር ልዩነት (Time Zone) ምክንያት ነው፡፡  

በዓሉ በሶብየት ሕዝብረት ውስጥ በተለዋወጡት ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ምክንያት በመሃል ቀዝቀዝ የማለት አዝማሚያ አሳይቶ ቆይቷል፡፡ እ.አ.አ በ1965 እንደገና 20ኛው የድል በዓል ሲታወስ ግን የወቅቱ የሶቭየት ሕብረት ፕሬዚዳንት ሊዮኒድ ብሬዥኔቭ ሙሉ ወታደራዊ ሰልፍ በማድረግ ትውፊቱን እንደገና አነሱ። ይህም ሜይ 9 እንደገና የሕዝብ በዓል ሆኑ እንዲሆን የተደረገበት ክስተት ነበር።

1985 እና 1990 የ40ኛው እና የ45ኛው ዓመት በግዙፍ ሰልፎች ተከብሯል፡፡ እነዚህ ክስተቶች ውስጣዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ዓለም አቀፋዊ ፀረ-ሾሳሊዝም በሰፈነበት ወቅት ሶቭየት ሕብረት የጦር አቅሟን ለዓለም ያሳየችበት ነበሩ።በሰልፎቹ የተደረጉት የድሉን ዐርበኞች በማክበር እና በቀዝቃዛው ጦርነት ምክንያት የተከሰተባትን ጫና መቋቋም እንደምትችል ወታደራዊ አቅሟን በማሳየት ላይ ነበር።

ከሶቭየት ሕብረት መፍረስ በኋላ ባሉት የ1990ዎቹ መጀመሪያዎች ላይ ወታደራዊ ሰልፎች በሩሲያ አልተካሄዱም ነበር። ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ዕለቱ በድምቀት እንዲከበር ማድረግ ጀመሩ፡፡ በ50ኛው ዓመቱ በ1995 በፕሬዝዳንት ቦሪስ የልሲን ዬልትሲን መከበሩ ግን ለበዓሉ መመለስ ወሳኝ ክስተት ነበር። ከ2000 መጀመሪያ እስከ አሁን በፕሬዚዳንት ፑቲን መሪነት በዓሉ በደማቅ ሰለፍ እየተከበረ ሲሆን፣ የሩሲያ ብሔራዊ ማንነት የማዕዘን ድንጋይ ተብሎ ይከበራል፡፡

ትዕይንቱ በሩሲያ ለድሉ አሸናፊዎች መታሰቢያ ከማድረግ ባለፈ የሀገሪቱን አቅም ማሳያ ሆኖ ያገለግላል። በሰልፎቹ የሩሲያን የኑክሌር ብቃት፣ እንደ T-14 Armata ያሉ ልዩ ታንኮች፣ የረቀቁ የጦር አውሮፕላኖች እና ጄቶች ይታዩበታል፡፡ ዜጎች "የማይሞት ሬጅመንት (Immortal Regiment)" የሚል ጽሑፍ ያረፈበት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዘመዶቻቸውን ፎቶግራፍ ይዘው ሰልፉ ላይ ይሳተፋሉ። ምዕራባውያን ሩሲያ ላይ ያላቸውን የተቃርኖ አስተሳሰብ እና ፋሺዝም የሚያወግዙ መልዕክቶች ይተላለፉበታል። ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ውጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከርም ይጠቀሙበታል።

እንደ ቻይና፣ ህንድ እና ሰርቢያ ያሉ ሀገሮች በመሪዎቻቸው ወይም በተወካዮቻቸው አማካኝነት በበዓሉ ላይ ይሳተፋሉ።የምዕራቡ ዓለም ሩሲያ ዕለቱን በመጠቀም የጠበኝነት ፖሊሲ ታራምዳለች በማለት ይወቅሷታል።

የሩሲያ ማኅበረሰብም በዓሉን እንደ ብሔራዊ ኩራት አድርጎ ነው የሚወስደው፡፡ የሩሲያ ትምህርት ቤቶች ታሪክን በስፋት ያስተምራሉ። ቤተሰቦች የቀድሞ አባቶችን ጀግንነት የሚያሳዩ ሜዳልያዎችን፣ ፎቶዎችን እና ታሪኮችን ያሳያሉ። የጦርነት መዝሙሮች፣ ፊልሞች እና ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ዊው በዓል ጋር አብረው ይከበራሉ።

የዘንድሮው 80ኛ ዓመት የሁለተኛ ዓለም ጦርነት መታሰቢያ እንደወትሮው በድምቀት እንደሚከበር ታውቋል፡፡ በዚህ በዓል ላይ የቻይና ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ከ20 በላይ የሀገራት መሪዎች እና ተወካዮቻቸው እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴም በዓሉ ላይ ለመታደም ሞስኮ ገብተዋል፡፡

ቤላሩስ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ካዛኪዝታን፣ አርሜኒያ፣ ኪርጊስታን እና የሶቭየት ሕብረት የቀድሞ አባላት የሆኑ ሀገራት ዕለቱን ሜይ 9 ብሔራዊ በዓል እድርገው ያከብሩታል፡፡ ከምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ፈረንሳይ ዕለቱን ብሔራዊ በዓል አድርጋ የምታከብር ሲሆን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፖላንድ እና ሌሎች ሀገራት ዕለቱን አስበውት ይውላሉ፡፡ ደቡብ ኮሪያ ደግሞ ኦገስት 15 ዕለቱን አስባ ስትውል፣ ቻይና ደግሞ ሴፕቴምበር 2 ታስበዋለች፡፡

አሜሪካ ሜይ 8 ዕለቱን አስባ ትውል የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ዕለቱ ብሔራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡

በለሚ ታደሰ 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top