ይህች ሴት ለ6 የዓለም ትላልቅ ክለቦች ተሰልፋ ተጫውታለች ። ሀገሯን ወክላ 100 ጨዋታዎችን አድርጋለች። 8 ቋንቋዎችን አቀላጥፋ ትናገራለች። በተለያዬ ጊዜ ትላልቆቹ ተቋማት ዕውቅናና ክብር ሰጥተዋታል ። ሽልማት አዝንበውላታል።
ናዲያ ናዲም የአፍጋኒስታን ምድር ያፈራት በአውሮፓ ደምቃ የዓለም ኮከብ መሆን የቻለች እንስት ናት፡፡
በአውሮፓውያኑ 1988 በአፍጋኒስታን ሄራት ከጦር ጄኔራል አባቷ እና የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ከሆነች እናቷ ተወለደች፡፡
ይቺው በተደላደለ ኑሮ በምቾት ተንደላቃ ያደገችው ጉብል በአንዲት ቀን ክስተት የወደፊት ሕይወቷ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተቀየረ።
የናዲያ አባት ጄኔራል ራባኒ ናዲም የአፍጋኒስታን ጦር የመሩ ወታደራዊ አመራር ነበሩ:: በአውሮፓውያኑ 2000 ታሊባን ሀገሪቱን ሲቆጣጠር ወደ በረሃ ተወስደው ተገደሉ፡፡
የጄኔራሉ አባቷ ሞት ሀዘን ብቻ አልወለደም የናድያ ቤተሰብን ዕጣ ፈንታ የቀየረ ክስተትም ሆነ እንጂ፡፡
በምቾት የኖረው ቤተሰብ ሁሉ ራሳቸውን ላለማሳወቅ ቀይረው በጭነት መኪና የአፍጋኒስታንን ድንበር አቋርጠው ለመሰደድ ተገደዱ፡፡
መዳረሻቸውን ሎንዶን አድርገው የተነሱት ስደተኞቹ ራሳቸውን በዴንማርክ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ አገኙት፡፡
ከሁለት ዓመት የስደተኞች መጠለያ ቆይታ በኋላ የጥገኝነት ጥያቄያቸው ይሁንታን አግንኝቶ የተረጋጋ ሕይወት መኖር ቢጀምሩም ለናዲያ ግን "አባቴ ከአሁን አሁን ይመጣል" የሚለው ጉጉት ለሁለት ዓመታት ያህል እረፍት ነስቷት ነበር፡፡
"15 ዓመት እስከሚሞላኝ ድረስ ምንም እንኳ በዴንማርክ ብንኖርም አባቴ ተመልሶ ይመጣል እያልኩ እጠብቀው ነበር" ስትል ከስፖርት ባይብል ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች፡፡
ከጦርነት ርቃ ልጅነትን እንደአዲስ ማጣጣም የጀመረችው ናዲያ በስደተኞች መጠለያ ከእህቷ እና ከሌሎች ልጃገረዶች ጋር እግርኳስን ቀናቸውን ለመግፊያ፣ ችግራቸውን ማሳለፊያ አድርገውት ነበር።
ቀኑ ጨልሞ እርስበርስ መተያየት እስከሚያቅታቸው ድረስ መጫወትን የዕለት ተግባራቸው አደረጉት፡፡
በዚህ የተጀመረው የእግርኳስ ጨዋታ በትምህርት ቤት ቆይታዋ ጎለበተ፡፡ የመጀመሪያ የክለብ ቆይታዋን ቢ ሃምሳ ሁለት አልቦርን በተባለ ክለብ ሀ ብላ ጀመረች፡፡
በ2008 የዴንማርክ ዜግነት ስታገኝ በልዩነት ከፊፋ በተገኘ ፍቃድ ዓለምአቀፍ ጉዞዋን በዚያ ጊዜ ጀመረች፡፡
ቀጥሎ 2006 እስከ 2012 በእኬ ስኮቭባኬን ቆይታዋ የሻምፒዮንስ ሊግ ስኬትን የስኮትላንዱን ግላስጎ ሲ 2 ለ 1 ባሸነፉበት ጨዋታዎች ሁለቱንም ጎል በማስቀጠር በድል ከፈተች፡፡
ወደ ኒዮርክ በማቅናት ለስካይ ብሉ ስድስት ጨዋታዎችን ተሰልፋ ሰባት ጎል አስቆጥራ ሦስት ለግብ አመቻችቶ በማቀበል የሳምንቱ ምርጥ ተጫዋች ለመባል በቅታለች፡፡
ቀጥሎ ፖርትላንድ ቶርንስን በመቀላቀል ዘጠኝ ጎሎችን በ20 ጨዋታዎች በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የግል ስኬቷን ተቀዳጀች::
ይህ ስኬት ክለቧንም የዓመቱ ሻምፒዮና ማድረግ የቻለ ሆነ::
2018 የማንችስተር ሲቲ ሴቶች ቡድንን በመቀላቀል በመጀመሪያ ጨዋታዋ ጎል በማስቆጠር ሬዲንግን እንዲያሸነፍ ስታደርግ በቀጣይ ጨዋታ ከቼልሲ ጋር ለነበረባቸው ጨዋታ የማሸነፊያ ብቸኛ ጎል ናዲያ መስቆጠር ችላለች፡፡
ምንም እንኳ በሄደችበት ሁሉ ስኬታማ መሆን መለያዋ ቢሆንም በማንችስተር ቆይታዋ ምቾት ያልተሰማት ናዲያ ቀጣይ ማረፊያዋን በፓሪስ ሴንጀርሜን አድርጋ በ2019 -20 የውድድር ዓመት ተሳተፈች።
በነበረው ቆይታዋም በ16 የሊግ ጨዋታዎች 13 ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡
በአንድ ክለብ ረጅም ጊዜ መቆየት የማይሆንላት ናዲያ በቀጣይ ሬሲንግ ልዩስቪሌ እና ኤሲሚላን እስከ 2024 የተጫወተችባቸው ክለቦች ለመሆን በቅተዋል፡፡
የነካሽው ሁሉ ይመርልሽ የተባለች የምትመስለው ናዲያ በተሰለፈችባቸው ቦታዎች ሁሉ ኮከብ ሆኖ መውጣት አይገዳትም። በዚህም ሀገሯን ዴንማርክን ወክላ 100 ጨዋታዎችን አድርጋለች፡፡
"ልጅ ሆኜ በምን ሙያ ውስጥ እንደምገባ ባላውቅም ስኬታማ እንደምሆን ግን አውቅ ነበር" ትላለች፡፡
አንዴ የገባችበትን ነገር በትጋት ወደ ስኬት መቀየር የምትችለው ናዲያ ከእግር ኳሱ በተጨማሪ በ2022 የሕክምና ዶክሬት ዲግሪ ተቀብላ የቀዶ ሕክምና ባለሞያም ሆናለች፡፡
8 ቋንቋዎችን አቀላጥፋ አቀላጥፋ የምትናገረው የናዲያን ስኬት የተገነዘቡ የተለያዩ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች በተለያየ ጊዜ ዕውቅና እና ክብር ቸረዋታል።
በ2018 ፎረብስ በዓለም አቀፍ ስፖርት ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ውስጥ 20ኛ ላይ አስቀምጧታል፡፡
የኢጣሊያው "ኮርዤረ ዴላ ሴራ" ዕለታዊ ጋዜጣ ደግሞ በ2024 የዓለም ምርጥ ሴት ዝርዝር ውስጥ አስፍሯታል፡፡
በተጨማሪም በ2019 ዩኔስኮ ለስፖርት እና ለጾታ ዕኩልነት ላበረከተችው ሚና እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለወጣቶች ፣ ልጃገረዶች እና ሴቶች በትምህርት ዘርፍ ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባሯ የልጃገረዶች እና ሴቶች ትምህርት ሻምፒዮና ብሎ ሰይሞ አምባሳደር አድርጓታል፡፡
ሀንዳይ ሞተርስ ከስኬታማ ሰዎች ጋር የሚሰራው ዓለም አቀፍ ፕሮግራም "ቲም ሴንቸሪ" አካል አድርጏታል::
በተስፋዬ ባዩ