የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በኢትዮጵያ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ቅርሶችን ጠብቆ ለማቆየት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የድርጅቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ሪታ ቢሶናውት ገለፁ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በኢትዮጵያ በትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
የዩኔስኮ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ተወካይ ሪታ ቢሶናውት (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ በርካታ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበች ሀገር ናት።
በዚህም እንደ ዩኔስኮ የኢትዮጵያ ተወካይ ኩራት እንደሚሰማቸው ጠቅሰው፣ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ተጨማሪ ቅርሶችን ለማስመዝገብ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የቅርሶች በዩኔስኮ መመዝገብ ቅርሶችን ለመንከባከብ እና ለመጠበቅ ከማስቻሉም ባለፈ፣ ቅርሶቹን የሚጎበኙ ሰዎችን ቁጥር ከፍ እንዲል በማድረግ የአካባቢው ማኅበረሰብ የቱሪዝም ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።
ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ሀብቶችን ለዓለም ማኅበረሰብ የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠራ ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ ያሉ ዲፕሎማቶች ቅርሶቹን እንዲጎበኙ የማድረግ ሥራ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ዩኔስኮ መንግስት በቅርስ ጥበቃና በሌሎች ዘርፎችም የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።