የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት የሚደረግባቸው ሀገራት የትኞቹ ናቸው?

1 Day Ago 2719
የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት የሚደረግባቸው ሀገራት የትኞቹ ናቸው?

ዜጎች ሕጋዊ የውጭ ሀገራት ስምሪትን በመከተል በሕገ-ወጥ ስደት ከሚደርስባቸው እንግልት እና መጭበርበር ራሳቸውን ሊከላከሉ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል። 

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴርም ዜጎች በሕገ-ወጥ መንገድ የሚያደርጉትን ጉዞ ማስቀረት የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑ ይታወቃል። 

ባለፉት 8 ወራት ከ309 ሺህ በላይ ዜጎች በውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አበበ ዓለሙ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል። 

በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት የዜጎችን መብት፣ ደኅንነት እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

በቤት ውስጥ የሥራ ስምሪት ላይ በስፋት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስፈፃሚው፥ በነርሲንግ፣ ኢንጅነሪንግ እና አሽከርካሪነት ላይ ያሉ ባለሙያዎችንም አሠልጥኖ የመላክ ሙከራዎች እየተደረጉ መሆኑንም አንሥተዋል። 

ይህንንም ለማጠናከር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2 ሺህ በላይ የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች በማቋቋም ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት። 

ተደራሽነትን ለማስፋት በማሰብ የበይነ መረብ ምዝገባ ማድረግ እና አስፈላጊ ሥልጠናዎችን መውሰድ እንደሚቻልም አቶ አበበ ገልጸዋል። 

አሁን ላይ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች፣ ጆርዳን፣ ኳታር እና ቤሩት የተቋሙ ሕጋዊ አጋር የሆኑ ሀገራት መሆናቸውን አመላክተዋል። 

“ከዚህ ውጭ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጩ የምናያቸው እና ሕጋዊ ያልሆኑትን በማጋለጥ ኅብረተሰቡ ለአላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት እንዳይዳረግ ሥራዎችን  ስንሠራ ቆይተናል” ብለዋል። 

ሆኖም ይህ ሥራ በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ዜጎች በየጊዜው ለተለያዩ ችግሮች እየተዳረጉ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል። 

ከላይ ባሉት ሀገራት በሚደረግ የውጭ ሀገራት ስምሪት ሕጋዊ በሆነው የሥራ አማራጭ ምንም ዓይነት ክፍያ እንደማይጠየቁም ነው ያነሡት። 

አሁን ላይ የግል የሥልጠና ተቋማትን ጨምሮ 309 የሥልጠና ተቋማት መኖራቸውን ገልጸው፣ ወደ ሀገራቱ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎች የመዳረሻ ሀገራቱን ባህል፣ ቋንቋ እና ሥራዎችን ይሠለጥናሉ ብለዋል። 

በሜሮን ንብረት እና አፎሚያ ክበበው


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top