በአውሮፓውያኑ 2025 የከተማው ህዝብ ወደ ስድስት ሚሊዮን እንደሚጠጋ ይገመታል:: ይህም በዓመት ከ4 በመቶ በላይ ያድጋል እንደማለት ነው።
በእንግሊዙ ኤክስፕረስ ድረ-ገጽ ላይ አምደኛው ክሪስ ቦራትየን እንዳስነበበው አፍሪካ የዓለምን ትኩረት መሳብ የጀመሩ ከተሞች መገኛ እየሆነች ነው ብሏል::
እነዚህ ከተሞች ደግሞ በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ውስጥ መሆናቸው ጉዳዩ ትኩረትን የሚስብ ሆኗል ነው የሚለው።
በድረ ገፁ ላይ ፀሐፊው ክሪስ ቦራትየን ከእንደነዚህ አይነቶቹ ከተሞች አንዷ ከባህር ጠለል በላይ በ2 ሺህ 355 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ነች ይላል።
ይህች ከተማ የአህጉሪቱ ከፍተኛ ዋና ከተማ መሆኗን የሚጠቅሰው ፀሀፊው በእንጦጦ ተራራ ስር ግርጌ የምትገኝ በተራሮችም የተከበበች ስለመሆኗ ምልከታውን አስፍሯል።
አዲስ አበባ በአፍሪካ ብቻም ሳይሆን በዓለም ደረጃ አራተኛዋ ከፍተኛ ዋና ከተማ መሆኗን ያስቀምጣል።
ምንም የከተማዋ አቀማመጥ ወደ ምድር ወገብ የቀረበ ቢሆንም አመታዊ አማካይ የሙቀት መጠኗ 18 ዲግሪ ሴሊሺየስ አካባቢ መሆኑ በአየር ንብረቷም ተወዳጅ ነች ብሏል።
የአፍሪካውያን መዲና አዲስ አበባ በአፍሪካ ትልቅ የከተማ ባቡር ያላት ስለመሆኗ የሚያነሳው ፀሀፊው፤ ማክሮትሬንድስ የተሰኘውን የመረጃ ምንጭ ዋቢ በማድረግ በ2025 የከተማው ህዝብ ወደ 6 ሚሊዮን እንደሚጠጋ ትንበያውን አስቀምጧል።
ከተማዋ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተመሰረተች ሲሆን በአውሮፓውያኑ 1889 የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ስለመሆኗም አትቷል::
ከዚህን ጊዜ ጀምሮ የፖለቲካ፣ የባህልና የኢኮኖሚ ዋና ማዕከል ለመሆን የበቃችው አዲስ አበባ ዛሬ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫ መሆኗን አንስቷል።
ከተማዋ የሀገሪቱ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች እና የውጭ ሀገር ሰዎች የሚኖሩባት መሆኗን የሚገልፀው ፀሀፊው፤ ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛ እና አረብኛም ጭምር የሚነገርባት መሆኗን አስቀምጧል።
በምልክቶቿ (ትእምርት) የምትታወቀው ከተማዋ በርካታ የቱሪስ መስህቦችንም ስለመያዟ አስነብቧል።
ብዙዎች የሚጎበኙት እና የሰው ዘር መገኛዋ ሉሲ የምትገኝበት ብሔራዊ ሙዚየም ቀዳሚ መሆኑን የሚገልፀው ፀሀፊው፤ ለተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ሁነት ዝግጅቶች የሚያገለግለው የመስቀል አደባባይም የከተማዋ መለያ መሆናቸውን አስፍሯል።
በ3 ሺህ 200 ሜትር ከፍታ ላይ ያለው የእንጦጦ ተራራ ደግሞ በእንጦጦ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን እና በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ቤተ-መንግስት መገኛነቱ ሌላኛው የመስህብ ስፍራ መሆኑን ይገልፃል።
የእንጦጦ ተራራ የአዲስ አበባን ሙሉ ገፅታ የሚያሳይ ከፍታ ቦታ ላይ መገኘቱ እና ለሃይኪንግ ወዳጆች ምቹ መንገድ መሆኑ እጅግ ተመራጭ እንደሆነም አንስቷል።
በኢትዮጵያውያን ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ቡና መሆኑን የሚጠቅሰው ፀሀፊው፤ አዲስ አበባም ቡና የት ልጠጣ ብሎ ለመቸገር እድል የምትሰጥ አይደችም ይላታል:: ምክንያቱም በየትኛውም አቅጣጫ ቡና ለመጠጣት የሚጋብዙ ካፌዎች ባለቤት ናትና ይላል::
ሌላው ተጨማሪው ነገር ይላል ፀሀፊው የአፍሪካ ግዙፍ የገበያ ቦታ መርካቶ መሆኑን ይገልፃል። በዚህ የገበያ ቦታ ተፈልጎ የሚታጣ አለመኖሩ እና ከትንሽ እስከ ትልቅ ሁሉም ነገር የሚገኝበት መሆኑ የቱሪስቶችን ቀልብ የሚይዝ መሆኑን አመላክቷል።