በአፈር ማዳበሪያ ላይ መንግሥት ድጎማ ባያደርግ እንዲሁም ታክስ እና ቀረጥ ቢታከልበት ኖሮ ዋጋው አሁን ካለበት ይልቅ እንደነበር የግብርና ሚኒስቴር ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሬዲዮ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭትን በተመለከ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከክልል የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓት አቅርቦት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ተስፋዬ የአፈር ማዳበሪያ ከስርጭት አንጻር ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚቀርቡበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በስርጭቱ ላይ በተደረገው ማሻሻ ችግሮቹ እየተፈቱ መሄዳቸውን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ አልፎ አልፎ ችግሮች ቢያጋጥሙም በሳምንት ሁለት ጊዜ ከክልሎች ጋር በሚደረግ ግንኙነት ችግሮች በፍጥነት እንዲፈቱ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአፈር ማዳበሪያ የሚገዛው ለመስኖ፣ ለበልግ እና ለመኸር ተብሎ እንደሆነ የጠቀሱት ኃላፊው፤ የክልሎቹ የዘር ወቅትም ቀድሞ ታቅዶበት በዚያው ሁኔታ ማዳበሪያው ቀድሞ እንደሚቀርብላቸው ገልጸዋል፡፡
በዚህ የምርት ዘመን 24 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ከክልሎች ጋር በመሆን ታቅዶ በዕቅዱ መሰረት እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ የዘንድሮ የአቅርቦት መጠን ካለፈው ዓመት በ4 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚልቅም ጠቅሰዋል፡፡
አቅርቦቱን ለማሻሻልም ዋናው ሥራ ግዢ መፈጸም መሆኑን ያነሱት አቶ መንግሥቱ፣ ለዚህም ከነሐሴ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ግዢው እየተፈጸመ እንደሆነ እና የማጓጓዝ ሂደቱም በተያዘለት መርሐግብር መሰረት እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት በበልግ ከ222 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቅሰው፣ የማዳበሪያ አቅርቦቱን ለመገምገም በቅርቡ በተለያዩ ክልሎች በተደረገ የመስክ ምልከታ በቂ የአፈር ማዳበሪ ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
አሁን እንደከዚህ ቀደሙ የአፈር ማዳበሪያ በሕገወጦች እጅ የመግባት ዕድሉ የመነመነ ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ በዚህ ድርጊት ላይ ሲሳተፉ በተገኙት ላይ የማያዳግም የእርምት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስርጭቱን የበለጠ ውጤታማ እና ከችግሮች የፀዳ ለማድረግ የሚያስችል መተግበሪያ እየተሠራ መሆኑን በመጠቆም፤ መተግበሪያው በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአፈር ማዳበሪያ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸው፤ መንግሥት ወደ ሀገር በሚገባው ላይ ድጎማ ባያደርግ እንዲሁም ታክስ እና ቀረጥ ቢታከልበት ኖሮ ዋጋው አሁን ካለው ይልቅ እንደነበር አመላክተዋል።
በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የግብዓት አቅርቦ ዳይሬክተር አቶ ታከለ ቁሩንዲ እንዳሉት፤ በክልሉ ሕገወጥነትን ለመከላከል የማዳበሪ ሽያጩ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ እንዲፈጸም ተደርጓል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስፈላጊውን የግንዛቤ ማስጨበጫ እንደተሰጠ የጠቀሱት አቶ ታከለ፤ በዚህ ምክንያት የስርጭት ሂደቱ እየተሻሻለ መምጣቱን እና በዚህ ዓመት ወደ 3 ሚሊዮን የአፈር ማዳበሪያ አርሶ አደሩ ጋር መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ስርጭቱን ለማሳለጥ አርሶ አደሩ ማዳበሪያውን ከሕብረት ሥራ ማኅበራት ብቻ እንዲወስድ ጥሪ ያቀረቡት ኃላፊው፣ የሕብረት ሥራ ማኅበራቱም ስርጭቱን በተያዘለት ጊዜ እንዲያፋጥኑ አሳስበዋል፡፡
በሲዳማ ክልል የተፈጥሮ ሐብትና የግብርና ግብዓት አቅርቦት ኃላፊ አቶ ለገሠ ሀንካርሶ በበኩላቸው፤ በክልሉ የማዳበሪ ሕገወጥ ሥርጭትን ለመከላከል እርምጃ እየተሰወደ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ከ138 የሚሆኑ ሰዎች በሕገወጥ የማዳበሪያ ስርጭት ምክንያት ወደ ሕግ ቀርበው ከአንድ እስከ አሥራ ስድስት ዓመታት የእስር ፍርድ እንደተላለፈባቸው አቶ ለገሠ ተናግረዋል፡፡
በለሚ ታደሰ