ዓድዋ ኢትዮጵያውያን ሊወርራቸው የመጣውን ጠላት በአንድነት መክተው አንገታቸውን በዓለም ፊት ቀና ያደረጉበት ግዙፍ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ድል ነው።
ትውልድ የየዘመኑ አሻራ እንዳለው ሁሉ ዓድዋን የቀደሙት ኢትዮጵያውን ደግሞም እነ አክሱምን፣ የሐረር ግንብን እና እነ ላሊበላን ሠርተው የሥልጣኔ ቁንጮዎች መሆናችንን አሳይተው አልፈዋል።
ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደኛ ጀምሮ ባለው የዓለም ሁኔታ ግን የኢትዮጵያውያን አሻራዎች እየደበዘዙ፣ እነአክሱምን የሠሩ እጆች ባዶ ቀርተው ይባስ ብለውም ለልመና ተዘረጉ።
ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ኢትዮጵያውያን የተፈጥሮ ሀብታቸውን ተጠቅመው ከችግር እንዳይወጡ የተደረገባቸው ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ ነበር።
የራስንም ችግር ነቅሶ ማውጣት ይገባልና ለሥልጣን ሲደረጉ የነበሩ የውስጥ ሽኩቻዎችም ሌላው ኢትዮጵያን እግር ተወርች ያሠራት ችግር ነው።
እናም ውኃ ላይ ተቀምጦ መጠማት እና አረንጓዴ አፈር ይዞ መራብ የኢትዮጵያ መገለጫ ሆነ። ጥንት ኃያል የነበረችው ኢትዮጵያ በግንባር ጦርነት ያሸነፈቻቸው ምዕራባውያንም ለርሃብ ተምሳሌት አድርገዋት በመዝገባ ቃላታቸው አሰፈሯት።
ታሪክን የቀየረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ
እስከ ቅርብ ጊዜ የዓባይ ውኃ ለግብፅ በረከቷ ለኢትዮጵያ ግን የእንጉርጉሮ ምክንያቷ ነበር። "ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል" በማለት ነው ዓባይን ማሳደር ያቃተው ትውልድ ሥነቃልን ያወረሰው።
መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ግን ዓባይ ማደሪያ ሊያገኝ የተወሰነበት እና ማደሪያውን ለማበጀት የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት ዕለት ነበር። መላው ኢትዮጵያውያንም ይቻላል የሚለውን ወኔ የታጠቁበት ታሪካዊ ዕለት።
ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የዓባይ ወንዝ ላይ ሊሠሩ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን ካስጠኑ በኋላ ጥናቱን ወደ ተግባር ለማስገባት በሩ ሁሉ ዝግ ሆነባቸው።
ሙከራቸው ሁሉ አልሳካ ሲልም እንዲህ በማለት አደራውን ለትውልድ አስተላለፉ፣ "እኛ ዓባይን እንገድብ ብንል አቅም የለንም፤ የውጭ ሀገራት ደግሞ ዓባይን ለመገደብ እርዱን ብንል ግብጥን ላለማስቀየም ፈቃደኞች አይሆኑም፤ ቀጣዩ ትውልድ በራሱ ገንዘብ ይገነባዋልና ጥናቱ በክብር ይቀመጥ!" በማለት ትንቢት መሳይ አደራ ለትውልድ አስቀመጡ።
ይህ ትውልድም አደራቸውን ለመረከብ ታደለ። ዳግማዊ ዓድዋን፣ የራሱን አክሱም፣ የአሻራውን ላሊበላ ለመገንባት የታደለው ትውልድ የዛሬ 14 ዓመት ጉባ ላይ የጀመረውን ርብርብ ከፍጻሜው ጫፍ አድርሶታል።
በርግጥ ፕሮጀክቱ ከዲፕሎማሲ ጫናው በተጨማሪ የውስጥ አሠራር ፈተናን ለማለፍም የተገደደበት ጊዜ ነበር። ግንባታው በተጀመረበት ፍጥነት ሒደት እንዳይጓዝ ያደረጉት በርካታ አሳሪ ሁኔታዎችም ነበሩ።
ከለውጡ በኋላ ግን እንቅፋቶች ሁሉ ተገርስሰው፣ ኢትዮጵያውያን ሕልማቸውን እንዲያሳኩ የሚያደርጉ አሠራሮች ተዘርግተው ዛሬ ላይ ግድቡን ወደማጠናቀቁ ተደርሷል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከግድብም በላይ የሆነ ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክት ነው። የወንዙ መገኛ ኢትዮጵያን ባይተዋር ያደረገው የተጣመመ ታሪክን ያቃና፣ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም በዓድዋ ነፃነታቸውን እንዳስከበሩ ሁሉ ድህነትንም ታሪክ በማድረግ ጠንካራዋን ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንደሚችሉ ያሳዩበት የመቻላቸው ሐውልት ነው።
ሕዳሴ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ከሚሰጣቸው ክንውኖች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ነው። ግድቡ የኢትዮጵያን ፍላጎት እና አቅም፣ ጠንካራ አቋም እንዲሁም የኢኮኖሚ ሽግግርን የሚያመለክት ነው።
ብሔራዊ ኩራት
ሕዳሴ በአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ነው። ይህ ግድብ በኢትዮጵያውን ላብ እና ጥሪት የተሠራ የኢትዮጵያውያን የጋራ አሻራ ነው።
ሕዳሴ እንደነ አስዋን ወይም እንደ ሌሎች ታላላቅ የአፍሪካ ፕሮጀክቶች በውጭ ዕርዳታ እና ብድር የተሠራ ሳይሆን ብርሃንን ለማየት የጓጉ ኢትዮጵያውን እናቶች ከመቀነታቸው አካፍለው የሠሩት የኩራታቸው ምንጭ ነው።
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ አመለካከት፣ በጎሳ እና በሌሎች ልዩነቶች ሳይከፋፈሉ በአንድነት እውን ያደረጉት ራስን የመቻል እና የልማት ራዕያቸው ማሳያ ነው።
የኢኮኖሚ ሽግግር ማሳኪያ ነው
ግድቡ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዕድገት፣ ሥራ ፈጠራ እና ኤሌክትሪክን ለሁሉም በማዳረስ ረገድ የኃይል ዋስትና እንድትሆን ያስችላታል። ከዚህም ባሻገር የኤሌክትሪክ የኃይል እንደ ሱዳን፣ ኬንያ እና ጅቡቲ ላሉት አጎራባች ሀገራት በመሸጥ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትሥሥሮችን ያጠናክራል። አልፎም የውጭ ምንዛሬን በማምጣት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ይደጉማል።
የሃይድሮ ፖለቲካ እና ዲፕሎማቲክ ተፅዕኖ
ግብፅ ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ እንዳታለማ ለዘመናት ጫና ስታደርግ ኖራለች። የኢትዮጵያ አቋም ደግሞ ሀሉንም በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ መንገድ መፈለግ ነው።
ግብፅ ለተቃውሞ ኢትዮጵያ ያልፈረመቻቸውን የቅኝ ግዛት ውሎች ስታነሳ ብትኖርም ይህ እንደማይሠራ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ አረጋግጣለች።
ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ በርካታ ጫናዎች ቢደረጉም ኢትዮጵያ ለጋራ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በሯን ሳትዘጋ ግድቧን ሠርታ ኃይል ማመንጨት ጀምራለች።
በዚህ አቋሟም ዓባይ የሦስት ሀገራት ሀብት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ተፋሰስ ሀገራት የጋራ ሀብት መሆኑን በማሳየት የዓባይን ጂኦ ፖለቲካ ቀይራለች።
የነገው ብርሃን
ግድቡ ለኢትዮጵያውያን መብራትም ኩራትም ነው። ኢትዮጵያ ዋነኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ላኪ እና የኢንዱስትሪ ማዕከል እንድትሆን ያግዛታል።
በአፍሪካ የኃይል አቅርቦት እና በዓባይ ተፋሰስ ዲፕሎማሲ ላይም ትልቅ ሚና እንድትጫወት በሩን ከፍቶላታል።
አረንጓዴ የኃይል ምንጭ በመሆን ዓለምን እያስጨነቀ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም እና በዚህ ረገድ ከራሷም አልፋ ለአፍሪካ እና ለዓለም ድርሻዋን እንድታበረክት ያስችላታል።
መውጫ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ገድብ ዓባይ ላይ የተሠራ አንድ ግድብ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያውያንን የማድረግ አቅም፣ ራስን መቻል ፍላጎት እና የመልማት ራዕያቸው ማረጋገጫ ነው። ግድቡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ የልማት፣ የኃይል እና የነፃነት መሪ ሆና እንድትወጣ የሚያስችላት ነው።
ሕዳሴ፣ ኢትዮጵያ ትላንት በዓድዋ ባስመዘገበችው አኩሪ ድል አፍሪካውያንን ለነፃነታቸው ትግል እንዳነቃቻቸው ሁሉ ዛሬም አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ መልማት እና ከድህነት መውጣት እንደምትችል ያሳየችበት ነው።
የኢትዮጵያውያን አንድነት ውጤት የሆነው ይህ ታላቅ ግድብ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጠናቀቅ እና በጋራ ሪቫን የሚቆረጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
በለሚ ታደሰ