ሚዲያ የፈጠራት እና እውነተኛዋ ብርቱካን

3 Days Ago 583
ሚዲያ የፈጠራት እና እውነተኛዋ ብርቱካን

ቤተሰብ የሠራት እውነተኛዋ ብርቱካን ባለትዳር፣ የቤት እመቤት ነች፤ መልካም የሚባል ትዳር ይዛም ከባንክ ሠራተኛው ከባለቤቷ ጋር አብሮ ይኖሩ እንደነበር በማስረጃ ተረጋግጧል፡፡

በኢቢኤስ ውስጥ የተፈጠረችው ብርቱካን ግን ከዚህ ተቃራኒ ነች፤ በጣም ብዙ ስቃይ ውስጥ ያለፈች፣ በርካታ ወንዶች ተፈራርቀው የደፈሯት እና ተደፍራ ለመውለድ የተገደደች፡፡

ቤተሰቦቿም አንዱን በስደት ሌላውን በሞት ተነጥቃ በሰው ቤት ተንከራትታ የተማረች ነች በፊልም የቀረበችው ብርቱካን፡፡

ፕሮግራሙ ላይ እናቷ እሷ የሦስት ዓመት ከ15 ቀን ልጅ እያለች በወሊድ ምክንያት በሆስፒታል መሞታቸውን እና አባቷ መሰደዳቸውን ትገልጻለች፤ እሷ ደግሞ ለወላጆቿ የመጀመሪያ ልጅ እንደሆነች ነበር የገለጸችው፡፡

እውነታው ግን ምንድን ነው?

እህቷ ማስተዋል ተመስገን ወላጆቻቸው ሠረቀ ብርሃን ቀበሌ ልዩ ስሙ ፅጌ ገሊላ በሚባል ቦታ አሁንም በሕይወት መኖራቸውን ትናገራለች፤ ብርቱካን ለቤተሰቧ ስድስተኛ ልጅ እንደሆነችም ነው ማስተዋል የምትናገረው፡፡

እሷም ለምን እንደዚህ እንዳደረገች ግራ እንደገባት እና ፊልሙን ተደውሎ ተነግሯት ከሌላው ሕዝብ ጋር እንዳየች በዚህም ግራ ገብቷት አይታ ለመጨረስ እንኳን እንደተቸገረች ትገልጻለች፡፡

ባለቤቷ አቶ ስማቸው ሹመት በበኩሉ አባቷ አቶ ተመስገን ከበደ፣ እናቷ ወ/ሮ ምንትዋብ ታመነ እንደሚባሉ ገልጾ፣ የእሱም የእሷም ቤተሰብ በሕይወት እንዳሉ ይናገራል፡፡

የእሱም የእሷም ቤተሰቦች ምሥራቅ ጎጃም ሠረቀብርሃን ቀበሌ አንድ አካባቢ እንደሚኖሩ የሚገልጸው ስማቸው፣ እሷ ከስምንተኛ እስከ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ሞጣ እንደተማረች ያወሳል፡፡

ከኢቢኤስ ፕሮግራም በኋላ እሷ ራሷ በሰጠችው ምስክርነት ደግሞ እናት እና አባቷ በሥርዓት አሳድገው ለቁምነገር እንዳበቋት እና በሕይወት እንዳሉ፤ መሞታቸው የተገለፀው ለትወና እንደሆነ ተናግራለች፡፡

ሁሉም ቤተሰቦቿ በሰላም እየኖሩ እንደሆነ እና እሷም ባለትዳር የሆነች እና የልጅ እናት መሆኗንም ትገልጻለች፤ የወለደችው ልጅም በሕጋዊ ትዳር የወለደችው እንጂ በእገታ እና በመደፈር የተወለደ እንዳልሆነ ገልጻ፣ ከዚያ ፕሮግራም ውስጥ እውነቱ የልብ ችግር እንዳለባት መነገሩ ብቻ ነው ትላለች፡፡

በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ላይ በተላለፈው ፊልም 12ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቀች ጥሩ ውጤት በማምጣቷ ሃረማያ ዩኒቨርሲቲ እንደደረሳት፣ በላይነሽ የምትባል ልጅ መኪና ላይ አግኝታ የት እንደምትሄድ ስትጠይቃት ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ደርሷት ወደዚያ እየሄደች እንደሆነ ነግራት እሷም ወደዚያ እንደቀየረች እና ፋርማሲ እንደተማረች ተናግራለች፡፡

ባለቤቷ ደግሞ 12ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቀች ሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ቢደርሳትም ከርቀቱም አንጻር ወደዚያ እንዳትሄድ ተደርጎ ሀዋሳ ዘመዶቿ ጋር እንድትማር መሄዷን ይገልጻል፡፡ እዚያም አካውንቲንግ መማሯን አክሎ ገልጿል፡፡

የስማቸው ዘመድ የሆነችው ፍቅራየሁ ደባስ እና አህቷ ማስተዋልም የተማረችው ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሳይሆን ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በእሁድ እና ቅዳሜ አካውንቲንግ መማሯን ምስክርነታቸው ሰጥተዋል፡፡

እሷ ከፕሮግራሙ በኋላ በሰጠችው ቃል በ2012 ዓ.ም 12ኛ ክፍል መፈተኗን የገለጸችበት እውነት በፕሮግራሙ ላይ ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ነበረች ከተባለበት ጊዜ በአንድ ዓመት የዘገየ ነው፡፡

ፕሮግራሙ ላይ ተደፈረች ተብሎ የተገለጸው ጊዜ አምስት እና ስድስት ዓመት እንደሚሆነው የሚገልጸው ባለቤቷ ስማቸው፣ ልጃቸው ሁለት ዓመት እንደሆነው እና ታሪኩ በራሱ የጊዜ ቀመር እንኳ የማይስማማ እንደሆነ ነው የገለጸው።

ፊልሙ መቼ እንደተሠራ ግራ እንደገባው የተናገረው ስማቸው፣ አብረው ሲኖሩ ምንም ዓይነት ጠባሳ እንዳላየባት ይገልጻል፤ ባንክ እንደሚሠራ እና ምንም ዓይነት ወደዚህ የሚያመራ ችግር እንደሌለም ተናግሯል፡፡

እህቷ ማስተዋል እና ጎረቤቶቿም ተቸግራ ነው እንዳይባል ምንም ዓይነት ለዚህ የሚያደርስ ነገር እንደሌላ ይናገራሉ፤ በተለይም እህቷ ከአቅም በላይ ቢቸግራቸው እንኳን የሚረዷቸው አጎቶች እንዳሏቸው አጽንኦት ሰጥታ ተናግራለች፡፡

ትዳር የመሰረቱ ኅዳር 2014 ዓ.ም እንደሆነ ነው የሚናገረው ስማቸው፤ ቤተሰብ ጋር ሄደው በሥርዓት እንደተዳሩ እና ለዚህም ሁሉም ማስረጃ እንዳላቸው ይገልጻል፡፡ እሷም ስማቸው የመጀመሪያው ባለቤቷ መሆኑን ገልጻለች፡፡

በለሚ ታደሰ 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top