የጤና ሚኒስቴር እና ኢትዮ ቴሌኮም የጤና ዘርፉን በዲጂታል ለማዘመን ተስማሙ

1 Day Ago 192
የጤና ሚኒስቴር እና ኢትዮ ቴሌኮም የጤና ዘርፉን በዲጂታል ለማዘመን ተስማሙ

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የተመራ ልኡካን ቡድን ጋር ሁለቱ ተቋማት በትብብር ለመስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

ዲጂታል ሄልዝ በጤና ሚኒስቴር ትኩረት ተሰጥቶት በጤና ፖሊሲ ውስጥ እንደተካተተ ያስረዱት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ ኢትዮ ቴሌኮም ለጤናው ዘርፍ እያቀረበ ስላለው የዲጂታል አገልግሎቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተ ልማትን በመጠቀም በማህበራዊ ሚዲያ የጤና ትምህርት እና ትክክለኛ የጤና መረጃ ለማህረሰቡ ማድረስ ተችሏል ያሉት ዶ/ር መቅደስ፤ ጤና ሚኒስቴር የቴሌ ሄልዝ አገልግሎት በፖሊሲ እንዲደገፍ እና በህጋዊ መንገድ እንዲመራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በጤና ተቋማት የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው፤ ኢትዮ ቴሌኮም የጤና ተቋማትን አሰራር በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በማዘመን፤ ለጤና ተቋማት የአገልግሎት ጥራትን መሻሻል ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የጤና ተቋማትን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የኔትወርክ እና የዲጂታል መሰረተ-ልማት ማስፋፊያ የሚያደርግበትን የቴክኖሎጂ አማራጮች መለየቱን አስረድተዋል፡፡  

በውይይቱ የጤና ሚኒስቴር እና ኢትዮ ቴሌኮም ወደፊት በአጋርነት ሊሰሩ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ላይ በሰፊው መክረው የጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top