የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ100 ዘመናዊ የብዙኀን ትራንስፖርት አውቶቡሶችን ዛሬ ሥራ አስጀምረዋል።
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ በአዲስ አበባ ያለውን የብዙኀን ትራንስፖርት እጥረትና የነዋሪዎችን እንግልት የሚቀንሱ 100 ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን በመግዛት ወደ ስምሪት ማስገባታቸውን ገልጸዋል።
አውቶብሶቹ የITS (ኢንተለጀንት የትራንስፖርት ሥርዓት) እና FCS (የታሪፍ ስብስብ ሥርዓት) ቴክኖሎጂን በተቀናጀ መልኩ በስራ ላይ ያዋሉ መሆናቸውንም አመላክተዋል።
አያይዘውም እነዚህ አውቶቢሶች ከአየር ብክለት ነፃ፣ ምቹ፣ በአንድ ጊዜ በርካታ የሠው ቁጥር ማጓጓዝ የሚችሉ፣ ዘመናዊና ተደራሽ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ አስተማማኝ፣ ለአውቶቡስ ብቻ በተፈቀደ መስመር ስለሚጓዙ ፈጣን አገልግሎት የሚሰጡ እንዲሁም ለነዳጅ ይወጣ የነበረውን ወጪ የሚቀንሱ ናቸው ብለዋል።
ወደ አገልግሎት የገቡት የኤሌክትሪክ አውቶቡሶቹ በዛሬው እለት በሁሉም የከተማዋ አቅጣጫዎች ለነዋሪዎች ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጡም ገልጸዋል።
የህዝባችንን እንግልት ለመቀነስ የጀመርነውን ራዕይ በመጋራት በመንግስትና የግል አጋርነት መርሃ-ግብር የመጀመሪያው የትራንስፖርት ኦፕሬተር በመሆን ዛሬ አገልግሎት መስጠት የጀመረውን የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ በነዋሪዎቻችን ስም ላመሰግነው እወዳለሁ ብለዋል ከንቲባዋ።