የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዱባይ ፖሊስ የምርመራ ቡድን ኃላፊ ሌ/ኮለኔል አብደላ መሃመድ ከተመራው የምርመራ ቡድን ጋር በወንጀል ምርመራ ዙሪያ ተወያይተዋል።
ኮሚሽነሩ ከወንጀል ምርመራ ቡድኑ ጋር ባደረጉት ውይይት በዱባይ ወንጀል ሠርተው በኢትዮጵያ የተሸሸጉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይ በሁለቱም ሀገራት ተፈላጊ የሆኑ ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ በመስጠት፤ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ በጋራ የወንጀል ምርመራ ቡድን በማቋቋም እና የልምድ ልውውጥ በማድረግ እንደሚሠራም ሁለቱ አካላት ተስማምተዋል።
ሌ/ኮለኔል አብደላ መሃመድ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ትብብር አመስግነው በቀጣይ ለሚከናወኑ የጋራ የወንጀል ምርመራ ሥራዎች ወደ ዱባይ የሚሄዱትን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ኃላፊዎች ለመቀበል ዝግጁነታቸውን እንደገለጹ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።