በአቶ አገኘሁ ተሻገር የተመራ ልዑክ በአለምአቀፉ ፓርላማ ህብረት ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ነው

11 Hrs Ago 99
በአቶ አገኘሁ ተሻገር የተመራ ልዑክ በአለምአቀፉ ፓርላማ ህብረት ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ነው

በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር የተመራ የፓርላማና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የልዑካን ቡድን በ150ኛው አለም አቀፍ የፓርላማ ህብረት (አይፒዩ) ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ኡዝቤኪስታን፣ ታሽከንት ከተማ ይገኛል፡፡

በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ ኢትዮጵያ በህብረቱ ውስጥ ያላትን አጋርነት አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

ለ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት አለማቀፍ ትብብሮችን ማጠናከር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግናን በአገር አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውን ለማድረግ ራዕይ ያላት አገር መሆኗን ያነሱት አቶ አገኘሁ፤ ሃገሪቱ ከ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች እና ከአፍሪካ አጀንዳ 2063 ጋር የተጣጣመ የ10 ዓመት አገራዊ የልማት ዕቅድ አውጥታ እየሰራች እንደምትገኝ አብራርተዋል።

ሃገሪቱ ባለፉት ተከታታይ አመታት ባደረገችው ጥረት ከ40 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም እንዲሳካ እየሰራች መሆኗን መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

የሚሊኒየሙ የዘላቂ ልማት ግቦች እንዲሳኩ ኢትዮጵያ የተለያዩ ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞችና የህግ ማዕቀፎችን መርምሮ በማፅደቅ፣ ክትትልና ድግፍ በማድረግ ፓርላማው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ድጎማ በጀት ለክልሎች የተመጣጠነ እንድገት በመመደብ ሥልጣን የተሰጠው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን እና የክልሎች የመሰረተ ልማት ስርጭት ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የመሠረታዊ ፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎትን በማስፋፋት ረገድ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጠንካራ የፓርላማ ቁጥጥር እና የህግ አውጭ እርምጃዎችን ለማሳደግ በቁርጠኛነት እየሰራች መሆኑንም ገልፀዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top