ኢትዮጵያ ቀድማ የጀመረችው የዓለም አቀፍ ገጠር ልማት እሳቤ

13 Hrs Ago 132
ኢትዮጵያ ቀድማ የጀመረችው የዓለም አቀፍ ገጠር ልማት እሳቤ

ኢትዮጵያ ቀድማ የጀመረችው የዓለም አቀፍ ገጠር ልማት እሳቤ

*******************

ሐምሌ 29 ቀን በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የገጠር ልማት ቀን የሚከበር ሲሆን፣ የዚህ ዓመቱም በዛሬው ዕለት በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ ይውላል።

ዕለቱ የገጠሩ ማኅበረሰብ የሚገጥመትን ፈተናዎች እና ተግዳሮቶች ዘላቂ በሆነ መልኩ በመፍታት ማኅበረሰቡ ለአጀንዳ 2030 ስኬት ያለውን ድርሻ ከፍ የሚያደርጉ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት ነው።

የዚህ ዓመቱ የዓለም የገጠር ልማት ቀን በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ዕውቅና ከተሰጠው ዓለም አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቀን ጋር መግጠሙ ደግሞ ልዩ ትርጉም አለው።

የኅበረት ሥራ ማኅበራት የገጠር ምጣኔ ሃብትን ለማነቃቃት እና የማኅበረሰቡን ቀጣይ ዕድገት እውን ለማድረግ ወሳኝ እንደሆነ ይታወቃል።

የኅበረት ሥራ ማኅበራት ለአካታች እና ለዘላቂ ዕድገት ያላቸውን አስተዋጽኦ የሚያጎላ ጭብጥ ያለው የዚህ ዓመት የዓለም የኅበረት ሥራ ማኅበራት ቀን፤ ማኅበራቱ የገጠሩን ማኅበረሰብ ሕይወት በዘላቂነት በመቀየር የገጠር ዓላማዎችን ያሳካል ተብሎ ይታመናል።

የዚህ ዓመት የገጠር ልማት ቀን "የገጠር ኃይል - ዓለም አቀፍ ተጽእኖ" በሚል ጭብጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅድሚያ የትኩረት አቅጣጫዎችን በማጉላት ይከበራል።

አብዛኛው የዓለም ድሃ ሕዝብ የሚኖረው በገጠር አካባቢ መሆኑን በመገንዘብ፤ በማኅበራዊ ጥበቃ፣ በመሬት ባለቤትነት እና በአመጋገብ የበለፀጉ የግብርና ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራትም አንዱ አቅጣጫ ነው። 

የገጠር አካባቢዎች የሚገጥማቸውን ከባድ የአየር ንብረት ተጽእኖ በአግሮኮሎጂ፣ ድርቅን በሚቋቋሙ ሰብሎች እና ውጤታማ በሆነ የውኃ አጠቃቀም በኩል መፍትሔ ማስገኘት ሌላው አቅጣጫ ነው። 

የገጠሩ ማኅበረሰብ በብሮድባንድ፣ በኢ-ዋሌት እና በገበሬዎች የመረጃ ማሰባሰቢያዎች አማካኝነት፤ የአገልግሎት እና የገበያ መዳረሻ ተጠቃሚ እንዲሆን ማመቻቸት ሌላው የገጠር ልማት እሳቤ ዓላማ ነው። 

የውርስ መብት ግንዛቤን ማስፋት፣ በሴቶች የሚመሩ የኅበረት ሥራ ማኅበራትን ማጠናከር እና የዲጂታል ክህሎት ሥልጠናዎችን ጨምሮ ምርት እና ምርታማነትን እንዲሁም እኩልነትን ለማሳደግ፤ አካታች ሥርዓት መፍጠር ሌላው የገጠር ልማት ቀን ዓላማ ነው።

እንደ መንገዶች፣ የመብራት ኃይል፣ ትምህርት እና የጤና መሰረተ ልማት ያሉ ወሳኝ ማኅበራዊ መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም የአካባቢን ሥነ-ምህዳር የጠበቁ ዘላቂ የግጦሽ ሥርዓቶችን ማበረታታት እና የአርብቶ አደር ማኅበረሰቡን በዘላቂነት መደገፍ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ማሳየት የዕለቱ ዓላማዎች ናቸው።

ዕለቱ እንዲከበር እ.አ.አ መስከረም 6 ቀን 2024 የተወሰነው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ነው። የዓለም የገጠር ልማት ቀን መመስረት፣ በገጠር ልማት ላይ ያተኮሩ እና በየአስርት ዓመታቱ የሚሻሻሉ ስትራቴጂዎችን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚረዳም ነው።

ይህም የገጠሩ ማኅበረሰብ ዘላቂነት ያለው የተሻለ ሕይወት እንዲኖር በማድረግ ረገድ ያለው ዓለም አቀፍ ቁርጠኝነት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የማሄዱ ማሳያ ነው።

ለሁለተኛ ጊዜ የሚታሰበው የ2025 የዓለም የገጠር ልማት ቀን ለሁሉም የተመድ አባል ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ እና ክልላዊ ድርጅቶች፣ እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ፣ የትምህርት እና የግል ዘርፍ ተግባራዊ ጥሪ ለማድረግ እንደሆነ ተመድ ዕለቱን አስመልክቶ ያዘጋጀው ሰነድ ያመላክታል።

ዘላቂ የገጠር ልማትን በማስፋፋት እና የገጠር ማኅበረሰብን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት ለማፋጠን፤ በዓለማ አቀፍ፣ በሀገር እና በክልል ደረጃ የተጣጣሙ የገጠር ልማት እንቅስቃሴዎች መኖር አለባቸው።

የገጠር ልማት በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ የገጠር ልማት ስትራቴጂዋን አሻሽላ ወደ ተግባር የገባችው ዓለም አቀፍ የገጠር ልማት ቀን ባለፈው ዓመት በተመድ ዕውቅና ከማግኘቱ ስድስት ዓመታት ቀደም ብሎ ነው።

የገጠር ልማትን ለዕድገት እና ለድህነት ቅነሳ ዋነኛ ሞተር መሆኑን በማመን፤ የዚህን ማኅበረሰብ ሕይወት ለማሻሻል ግብርናን በማዘመን ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው። 

እንደ አረንጓዴ አሻራ፣ የስንዴ ኢኒሼቲቭ እና የገጠር የፋይናንስ ተዳራሽነት ያሉ አዳዲስ እርምጃዎች የአየር ንብረት ለውጥን ተቋቁሞ ምርታማ የሚሆን የገጠር ማኅበረሰብ ለመፍጥር ያለሙ ናቸው። 

ምርታማነትን ለማሳደግ የምርት ግብአቶችን ከማቅረብ በተጨማሪ፤ ተበጣጥሰው ምርታማነታቸው የቀነሱ መሬቶችን በኩታ-ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በማረስ ውጤት እየተገኘበት ነው። 

ከዚህ በፊት ተረስተው የነበሩ ሰፋፊ ለም መሬቶችን ወደ ምርት የማስገበት እንቅስቃሴም የተጀመረ ሲሆን፣ ሶማሌ እና አፋር ክልሎች ለዚህ ማሳያዎች ናቸው። 

ሌላው የገጠሩን ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት በማሳደግ የኢትዮጵያን ዕድገት ያረጋግጣል ተብሎ የሚጠበቀው በቅርቡ የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት ነው። 

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የሆነው የገጠር ኮሪደር ልማት የገጠሩ ማኅበረሰብ ዘመናዊ አኗኗርን እንዲለማመድ ከማድረግ የተሻገረ ጠቀሜታ ይኖረዋል። 

የመብራት፣ የመንገድ እና የፋይናንስ አገልግሎቶች እየሰፉ ሲሄዱ፣ የእንስሳት እና ሰው ማደሪያ ሲለያዩ ጤናማ እና ንቁ የገጠር ማኅበረሰብ ለመፍጠር ያስችላሉ። 

የገጠሩ ማኅበረሰብ ጽዱ አካባቢን እየፈጠረ በመጣ ቁጥር ምርት እና ምርታማነቱም በዚያው መጠን እየጨመረ ይሄዳል፤ ከነባራዊ ዓለም ጋር ስለሚሄድም አስተራረሱን ወደ ሜካናይዜሽን አልፎም ወደ ኢንዱስትራላይዜሽን ያሳድጋል።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top