"ክርስቶስ ከሙታን እንደተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሣም ማለት ነው፡፡ ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፡፡ እምነታችሁም ከንቱ ነው ደግሞም እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በመመስከራችን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል" (1ቆሮ 15፤13-15)
በክርስቶስ የተወደዳችሁ ብፁዓን ጳጳሳት
ክቡራን ካህናት፤ ገዳማውያንና ገዳማውያት
በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች
የእግዚአብሔር ሕዝቦችና ምዕመናን
በተለያየ ምክንያትና ሁኔታ ከአገራችሁ ውጪ የምትገኙና የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምዕመናን በሙሉ
ቸርነቱ የማያልቅበት አምላክ ሁላችንንም በሰላም ጠብቆ እንኳን ለ2017 ዓ.ም ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሰን!
የትንሣኤ በዓል የክርስቲያን ሕይወት መሠረትና ምሶሶ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ትንሣኤ ባይኖር እምነታችን ከንቱ በሆነ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ የሚታዘንልን ሰዎች በሆንን ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክቱን የጻፈው በቆሮንጦስ ክርስቲያኖች መካከል ትንሣኤን የሚጠራጠሩ ሰዎች ስለነበሩ ነው፤ በሌላ አነጋገር ትንሣኤን እየካዱ ወይንም እየተጠራጠሩ ክርስቲያን ነን ማለት ትርጉም እንደሌለው እያስተማረ ነበር ማለት ነው፡፡
ሰውን በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረ ጌታ አሁንም ሰውን በትንሣኤው አዲስ ፍጥረት አደረገው፡፡ ሰውን በመልኩና በአምሳሉ መፍጠሩ ብዙ ያስተምረናል፡፡ የተለየ ቦታና ሃላፊነት ለሰው እንደተሰጠ ያሳየናል፡፡ ትንሣኤው ደግሞ ሰውን በሙሉ በድጋሚ ወደ አንድ ማምጣቱን ያሳየናል። ትንሣኤ በሰው ውድቀት የተጨማደደውን መልክ ያስተካክላል፡፡ ትንሣኤ ሁሉንም ነገድ፤ ሁሉንም ቋንቋ፤ ሁሉንም ባህል ወደ አንድ ያመጣዋል፡፡ ትንሣኤ የጎደለውን ይሞላል፡፡ የተረሳውን ያስታውሳል፡፡ የሕይወትን ወሳኝ ጥሪ ወደ ትክክለኛው ቦታ ይመራዋል፡፡ የትንሣኤዉ የምሥራች ከምንም በላይ የምርምር ውጤት ሳይሆን የእምነት ፍሬ ነገር መሆኑንም ማስተዋል ያሻል፡፡ ትንሣኤን መስበክ የተቀበሉትን እምነት ማስተላለፍ ነውና፡፡
ቅዱሳት መጽሐፍ ስናነብና ስናሰላስል በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ብርሃን የምናይበት ወቅት ያስፈልገናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሰውን ልጅ ታሪክም ሆነ የራሳችንን ታሪክ እንዲሁም በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ብርሃን ልንቃኘው ያሻል፡፡ በዚያን ወቅት አዲስ መረዳትን እናገኛለን፡፡ ዘመናችንን በልዩ ብርሃን እንረዳለን፡፡ የታሪክ ትርጉማችንንም ይቀይራል፤ ለሕይወትም የምንሰጠው ትርጉም ሙላትና በረከት ይኖረዋል፡፡ ምናልባት መልስ ያጣንባቸው እንቆቅልሾች መልስ ያገኛሉ፡፡
ሐዋርያት ክርስቶስን እስከ ቀራንዮ ድረስ መከተል ከብዷቸው ሸሽተው ነበር፡፡ በድፍረት ወጥተው መመስከር የቻሉት በትንሣኤውና በጰራቅሊጦስ ምስጢር የተነሣ ነው፡፡ ቀራንዮና የመስቀል ሞት ያለትንሣኤ አሁን ያለውን ትርጉም ባላገኙ ነበር፡፡ የወንጌል የምሥራች የተገለጠው በክርቶስ ትንሣኤ ነው፡፡
ብዙ የሚያስጨንቁና የሚያሳዝኑ ነገሮች በዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ ያጋጥሙናል፡፡ የሰው ጥበብ እስከተወሰነ ድረስ ያደርሰን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጌታችንን በመከተል ብቻ የሚገኙ በረከቶች አሉ፡፡ የተፈጠርንበትን ዓላማ ስንስት ወደ መሠረታዊው ዓለም የሚመልሰን ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ መከፋፈል፣ መድሎ፣ ምቀኝነት፣ ጭካኔ የተፈጠርንበት ዓለም አይደሉም፡፡ አፍራሽ ሐሳብ፤ ጎጂ ንግግርና ተግባር ከተፈጠርንበት ዓላማ እጅግ የራቁ ነገሮች ናቸው፡፡ እውነተኛ መፍትሔዎች የሚመጡት ከእግዚአብሔር ነው፡፡
ወደ መስቀሉ ስንቀርብ ወደ ትንሣኤውም እንቀርባለን፡፡ መስቀል መሸሸጊያችን ሲሆን ትንሣኤም እንዲሁ አምባችን ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በመስቀልና በትንሣኤው አማካኝነት አዲስ ኪዳንን፤ አዲስ ፍጥረትን፤ እውነተኛ እርቅን አምጥቷልና ነው፡፡
በመስቀልና በትንሣኤው የተሰበረው ይጠገናል፤ የደከመው ይበረታል፤ የወደቀው ይነሣል፤ የተሸነፈው ያሸንፋል ይህንንም ለማክበር በትንሣኤው እንሰበሰባለን፡፡ የአምልኮ ሥርዓታችን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ የተመሠረተ ነውና፡፡ መስዋዕተ ቅዳሴ በመስቀልና በትንሣኤው አዲስ ፍጥረት መሆናችንን የምናከብርበት በዓል ነው፡፡
ትኩረታችን ወዴት ይሆን? ወደ አዳምና ወደ ሔዋን ወይንስ ወደ አዲሱ አዳም ክርስቶስና ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም? ወደ ቃየልና ወደ አቤል ወይንስ ወደ ቅዱሳን ሰማዕታት? በበለጠ ግን ከአዲሱ አዳም ከክርስቶስ መለኮታዊ ፍቅርንና ትንሣኤን እናገኛለን፡፡
በመስቀሉና በትንሣኤው እግዚአብሔር እራሱን ከዓለም ጋር አስታርቋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም የማስታረቅን ምስጢር በሰፊው አስተምሯል፡፡ ክርስቲያን የዚህ የዕርቅ መሣሪያ መሆኑን ገልጾልናል፡፡ በምድር ላይ ያሉ ውብ ነገሮች እውነተኛውን ውበት የሚላበሱት በትንሣኤው ብርሃን ነው፡፡ የተስፋ ጭላጭል ደምቆ የወደፊቱን የሚገልጠው የፍቅር እሳት ከጫፍ እስከ ጫፍ ተስፋፍቶ የሚቀጣጠለው የእምነት ብርሃን ጠቢባንን የሚወልደው በትንሣኤው ብርሃን ነው፡፡
በዚህ በትንሣኤ በዓል መላው ምዕመናን ልናደርገው የሚገባን የተቸገሩትን ወገኖች በመርዳትና በመተሳሰብ፤ ያዘኑትን በማጽናናትና በማሰብ እንድታከብሩና ደስታቸውንም ፍፁም እንድታደርጉ ፀጋችሁንም እንድታበዙ አደራ ማለት እወዳለሁ፡፡
ዘንድሮ በእግዚአብሔር ቸርነት የኒቂያ ጉባኤ የዛሬ 1700 ዓ.ም. በወሰነው መሰረት ክርስቲያኖች በመላው አለም በህብረት የትንሳኤን በዓል ያከብራሉ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለክርስቲያኖች ህብረት ሲናገር ክርስቲያኖች ሁሉ አንድ ይሆኑ ዘንድ ብሎ ጸልዮ ነበር። አሁንም በዚህ የትንሳኤ በዓል ክርስቲያኖች በህብረት በአንድነት የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤ በዓል ለማክበር በቅተናልና ወደፊትም ይህ እንዲደገም ክርስቲያኖችም በህብረት በዓሉን ማክበር እንዲችሉ ጸጋውን በረክቱን እንዲሰጠን እንድትጸልዩ አደራ እላለሁ።
በመጨረሻም በየቤታችሁና በየሆስፒታሉ የምትገኙ ህሙማን እግዚአብሔር እንዲምራችሁ፤ በስደትና በመፈናቀል ሁኔታ ውስጥ ያላችሁትን ወገኖች እግዚአብሔር ለአገራችሁና ለቄያችሁ እንዲያበቃችሁ፤ በየማረሚያ ቤት ያላችሁትን ታራሚዎችንም እግዚአብሔር እንዲያስባችሁ በመመኘት እንኳን ለበዓለ ትንሣኤው አደረሳችሁ፡፡
የሰላም ባለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓሉን የደስታና የምሕረት በዓል ያድርግልን፡፡ ለህዝቦቻችንና ለአገራችንም ሰላሙን ይስጥልን፡፡
እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያን ለዘለዓለም ይባርካት!