ከታሪፍ በላይ በማስከፈልና ትርፍ በመጫን ህዝብን ያማረሩ 247 ግለሰቦች ርምጃ ተወሰደባቸው

17 Hrs Ago 132
ከታሪፍ በላይ በማስከፈልና ትርፍ በመጫን ህዝብን ያማረሩ 247 ግለሰቦች ርምጃ ተወሰደባቸው

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከአስሩም የክላስተር ከተሞች ተነስተው ወደ አዲስ አበባ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት ሕግ እና ሥርዓት ያላከበሩ 247 ግለሰቦች ላይ ርምጃ መወሰዱን የክልሉ የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ገለፀ፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የመሰረተ ልማት አስተባባሪና የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ኑሪዬ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ዶትስትሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በተወሰደው ርምጃ 14 የአሽከርካሪዎች ማህበራት ተቀጣሪዎች መባረራቸውን ተናግረዋል፡፡

10 የስምሪት ባለሙያዎችና ሌሎች የትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያዎች የእርምት ርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

 

ትርፍ በመጫን ተሳፋሪውን ማመናጨቅ፣ ከመንገድ ላይ ማውረድ ከመነሐሪያ ውጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የሚታይ ሥርዓት አልበኝነት እና የሥነ ምግባር ጉድለት መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ይህን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ በመሆኑ ተጠቃሚው በ8934 ነጸ የስልክ መስመር ላይ በመደወል ቅሬታውን እንዲያቀርብ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ርምጃ የተወሰደባቸው ሌሎች ግለሰቦች ከታሪፍ በላይ በማስከፈልና ትርፍ መጫን ላይ ተሰማርተው እንደነበርም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

ሕግ እና ሥርዓት አክብረው የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ ተሳፋሪውን የሚያጉላሉ በርካቶች መሆናቸውን ያወሱት ኃላፊው፣ የቁጥጥር ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግም የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት በክልሉ በሚገኙ 10 የክላስተር ከተሞች መተግበሩን አንስተዋል፡፡

በሆሳዕና፣ ወራቤ፣ ቡታጂራ - አዲስ አበባ መስመር የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች የሚያነሷቸው ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ ትርፍ መጫን እና ተገልጋዩን ማንገላታት ቅሬታ መኖሩን ጠቅሰው፤ የክልሉ ትራፊኮች ቁጥጥር የላላ መሆኑ ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ትራፊክ ፖሊሶች ገንዘብ እና እጅ መንሻ እየተቀበሉ ለተሳፋሪው ምንም ሳይጨነቁ መኪናውን እና አሽከርካሪውን ሳይቆጣጠሩ የሚያሳልፉበት መንገድ መኖሩን መታዘባቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ይህን የአገልግሎት ችግር በዛላቂነት ለመፍታት በቅንጅት መሠራት እንዳለበት የገለጹት ኃላፊው፣ ማህበረሰቡን በማንቃት እና የቁጥጥር ሥርዓቱን ይበልጥ በማጠናከር ሕግ የማያከብሩትን ሥርዓት የማስያዙ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በመሀመድ ፊጣሞ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top