ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፓትሪያርኩ በመልዕክታቸው፣ በመላው ኢትዮጵያ በገጠር እና በከተማ ለሚኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር ለሚገኙ፣ የሀገርን ዳር ድንበር ለመጠበቅ እና ለማስከበር በየጠረፉ ለቆሙ፣ በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ላሉ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆነው በየማረሚያ ቤቱ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያት በሙሉ፣ “በትንሣኤው የሕይወት መንገድን ያሳየን ጌታችን አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለ2017 ዓ.ም በዓለ ትንሣኤው በሰላም አደረሰን፤ አደረሳችሁ!” ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ሕይወት በዓለመ ፍጡራን ውስጥ ከሚገኘው ድንቅ ነገር ሁሉ ተወዳዳሪ የሌላት ድንቅ ነገር ናት፤ ሕይወት ኣካልን የማንቀሳቀስ፣ የማመዛዘን፣ የመወሰንና የመስራት ሀብተ ጸጋ ያላት ልዩ ፍጥረት ናት።
በዚህም ምክንያት ሕይወት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ወይም የሚመስል ጠባይ ኣላት፤ ሰው የእግዚአብሔር መልክና ኣምሳል ኣለው የሚለው መጽሓፍ ቅዱሳዊ ኣስተምህሮም ከዚሁ ጋር የሚስማማ ነው፤ ሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ የተጣበቀ ወይም የተሳሰረ ግንኙነት ኣላት፤ “ወኅብእት ሕይወትክሙ ምስለ ክርስቶስ፡- ሕይወታችሁ ከክርስቶስ ጋር የተሳሰረች ናት” የሚለው ሐዋርያዊ አባባልም ይህንን ያመለክታል።
ሕይወት ፈጣሪንና የፈጣሪ ርዳታን ስትሻ የመኖርዋ ምስጢርም ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝ ጸጋ ስላላት ነው፤ ሕይወት መልካም ስትሰራ ደስተኛ፣ ክፉ ስትሰራ ደግሞ ስቅቅተኛ የምትሆንበት ምክንያትም ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኛት ጸጋ ስለሚነግራት ነው። ምክንያቱም መልካምን መውደድ፣ ክፉን መጥላት የእግዚአብሔር የማይለወጥ ጠባይ ስለሆነ፣ ክፉን ሰርታ ከእርሱ ጋር በደስታና በነጻነት መኖር በፍጹም ኣትችልምና ነው።
የመጀመሪያው ሰው ኣዳም ክፉውን ከሰራ በኋላ ወዲያውኑ መሸሸግና መደናገጥ ሊወረው የቻለው ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላት ውሳጣዊት ሕይወቱ ከእግዚአብሔር ጋር ኣብራ መቀጠል የማትችልበት ደረጃ እንደደረሰች ስለተረዳች ነው። ከዚህ ኣንጻር ሕይወት የመኖር ጸጋ ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ተሳስሮ የመኖር ጸጋም ያላት መሆኑን እንገነዘባለን።
ሕይወት የማትጠፋ ብትሆንም የመሞት ስጋት ያልተለያት ፍጡር ናት፤ በተለይም እግዚአብሔርን የበደለች ዕለታ ከባድ የሞት ኣደጋ ያጋጥማታል፤ ይህም ሞት የሥጋ ሳይሆን ከእግዚአብሔርና የእግዚአብሔር ከሆነው ሁሉ መለየት ነው፤ የሕይወት ከባዱ ሞትም ይኽ ነው።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
እኛ ሰዎች በኃጢኣት ጠንቅ ያጣነው ሕይወት እንዳለ ቅዱስ መጽሓፍ “በኣንድ ሰው በደል ኃጢኣት ወደ ዓለም ገባ፤ በዚህም ምክንያት ሰው ሁሉ ሞተ ወይም ከእግዚአብሔር ተለየ” በማለት የእኛ ከእግዚአብሔር መለየት ዋናው ሞት እንደሆነ ያስረዳል።ይህ ገለጻ ከእግዚአብሔር ጋር የመኖር ሕይወታችን በበደል ምክንያት ማጣታችንን የሚያሳይ ነው። እኛ በደለኞች ሆነን ከእግዚአብሔር የተለየንበት የመጀመሪያው ምክንያት በደለኞች ከሆኑ ኣዳምና ሔዋን የተገኘን መሆናችን ነው።
በመሆኑም የሁላችንም ሥጋዊና መንፈሳዊ ኣካል የተከፈለው ከነሱ እንደመሆኑ መጠን ያለን ሁሉ እንደነሱ ቀድሞውኑ የሞተና የተፈረደበት ነው። በሌላ ኣባባል በጥንተ ኣብሶ ምክንያት ከእግዚአብሔርና የእግዚአብሔር ከሆነው ሁሉ የተለየን ሆን ማለት ነው፤ ስለዚህም ነው በኣንድ ሰው በደል ምክንያት ሁሉም ሞቱ ብሎ እግዚአብሔር ያሳወቀን፤ ጥንተ ኣብሶ ወይም የውርስ ኃጢኣት የሚባለውም ይኽ ነው።
ከዚህም ጋር ከእግዚአብሔር የለየን የውርሱ ኃጢኣት ሳይበቃን በየሰዓቱ በምንፈጽመው ክፉ ተግባር በበደል ላይ በደል እየጨመርን በመቀጠላችን በጨለማ ላይ ተጨማሪ የጨለማ ጥላ ኣክለንበታል። ይህ ሁሉ ተደማምሮ ሞታችን ወይም ከእግዚአብሔር መለየታችን የሰፋና የከፋ እንዲሆን ኣድርጎታል፤
የተወዳዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናትና ምእመናት!
ከእግዚአብሔር የለያየን ኣበሳ - ኃጢኣት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ከባድ ቢሆንም እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ያለው ፈቃድ በተስፋ ጭላንጭል ማሳየቱን ኣላቋረጠም። ይኸውም የበደላችን ዕዳ ከመጀመሪያው ኣንሥቶ የማዳን ተስፋውን በተነገረለት በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ ሞት እንደሚሰረዝ፣ በእርሱም ጽድቅ እንደ ጻድቃን ተቈጥረንና ያጣነውን ሕይወት እንደገና ኣግኝተን ወደ እግዚአብሔር እንደምንቀርብ፣ ይህም ከትንሣኤ በኋላ እውን እንደሚሆን እግዚአብሔር ለእኛ ደጋግሞ ይፋ ኣድርጎኣል።
ይህንን ተስፋ - ትንሣኤ በመንፈስ ቅዱስ የተረዳ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በምስጋና መዝሙሩ እንዲህ ብሎ ይገልጸዋል፤ “ዳግመኛም ሥጋዬ በተስፋው ኣደረ፤ ነፍሴን በመቃብር ኣትተዋትምና፤ ጻድቅህንም በመቃብር ተጥሎ፤ ፈርሶና በስብሶ ይቀር ዘንድ ኣሳልፈህ ኣትሰጠውም፤ የሕይወትንም መንገድ እንዲህ ኣሳየኸኝ” በማለት የሕይወታችን ተስፋ-ትንሣኤን በሚያስደንቅ ኣገላለጽ ኣስረድቶናል።
ገለጻው የክርስቶስንና የኛን ትንሣኤ እንደሚመለከት በቅዱሳን ሓዋርያት ተርጓሚነት በቅዱስ መጽሓፍ ተብራርቶ ይገኛል። በመሆኑም የእኛ መጨረሻ የሚጠናቀቀው በመቃብር ተጥሎ፤ ፈርሶና በስብሶ በመቅረት ሳይሆን እንደገና ተነሥቶና ከእግዚአብሔር ጋር በተሳሰረ ኃይለ ሕይወት ለዘላለም በመኖር እንደሆነ ቃሉ ያስረዳናል። ቅዱስ ዳዊት ከትንሣኤ በኋላ የሚሆነውን ይህን ጣዕመ ሕይወትን ነው ኣሳየኸኝ ብሎ የገለጸው፤ ጌታችን የዚህ ሕይወት የትንሣኤ በኵር ሆኖ ተነሥቶኣል፤ ከትንሣኤውም በኋላ ለዘላለም በሕይወት ይኖራል።
በቀጣይም ጊዜው ሲደርስ እኛ ተከታዮቹ የእርሱን ዓይነት ትንሣኤ ተነሥተን በማያልቅ ኃይለ ሕይወት ከሱ ጋር ለዘላለም በሕይወት እንኖራለን፤ ጌታችን ያሳየን የሕይወት መንገድ ይኸው ነው። ይኽ ሕይወት ከሁሉም ህላዌ - ሕይወት የላቀና የበለጠ ጣዕም ያለው ዘላለማዊና ድንቅ ሕይወት ነው፤ ይኽ ሕይወት ከስጋት፣ ከስሕተት፣ ከቅጣትና ከሞት - ፍርሓት ነጻ የሆነ፣ በፍጹም ነጻነትና ደስታ ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም የሚያኖር ሕይወት ስለሆነ ሁላችንም ወደዚህ ሕይወት ለመድረስ በእምነት እንተጋለን።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
ዘር ሳይኖር ፍሬ እንደማይገኝ ሁሉ ሕይወታዊ ትንሣኤም ያለ ሃይማኖትና ሥነ - ምግባር ሊገኝ ኣይችልም። ጌታችንም ይህንን ኣስመልክቶ ሲያስተምረን “መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ይነሣሉ፤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ›› ብሎ ኣሳውቆናል።
ከዚህ አኳያ የሕይወትን ትንሣኤ የሚያገኝ ያመነ፣ የተጠመቀና መልካም ስራን የሰራ እንጂ የተነሣው ሁሉ ኣለመሆኑ ግልጽ ነው፤ መነሣቱ ሁሉም የግድ ይነሣል፤ ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ የሚጠብቀን ሕይወት በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ ሳለን በሰራነው ስራ የሚወሰን እንደሆነ ጌታችን በማያሻማ ሁኔታ ኣረጋግጦልናል።
ስለሆነም የመጨረሻው ዕድላችን የተንጠለጠለው እምነትን ተከትለን በምንሰራው ስራ ላይ መሆኑን ለኣፍታ እንኳ መዘንጋት የለብንም፤ ዛሬ ከሰው ኣእምሮ በእጅጉ እየራቀ የሚገኘው ይኸው እምነትና ሥነ-ምግባር ነው፤ ሰዎች ከእምነትና መልካም ሥነ-ምግባር በራቁ ቊጥር ሕይወት መራራ እንድትሆን ትገደዳለች።
እኛ ኢትዮጵውያን ከጥንት ጀምሮ በእምነትና ሥነ-ምግባር እየተመራን፣ በደልን በይቅርታ እየዘጋን፣ እስከ ጋብቻ በሚዘልቅ ባህለ-ዕርቅ ደምን እያደረቅን፣ በወንድማማችነት ፍቅር ተስማምተን በሺሕ ለሚቆጠሩ ዘመናት እንዳልኖርን፣ እነሆ ዛሬ ለታላቅነታችን በማይመጥን ሆናቴ መለያየትና መጣላት ብሎም እርስ በርስ መገዳደል ዕለታዊ ተግባራችን ኣድርገን እንገኛለን።
ይህ በጣም ኣሳዛኝ ክሥተት ነው፤ ይህንን ሳናስተካክል የምናከብረው በዓለ ትንሣኤም እዚህ ግባ የሚባል ደስታ ሊያስገኝልን እንደማይችል የታወቀ ነው። እየሆነ ያለው ሁሉ ማንንም ኣይጠቅምም፤ በዕርቅ፣ በይቅርታና በውይይት የማይፈታ ችግር ያለ ይመስል ይህን ያህል መጨካከን እንዴት እንደ መፍትሔ ተደርጎ ይወሰዳል? አሁንም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን የምንማፀነው፡- እባካችሁ እኛው ራሳችን ሸምጋይና ተሸምጋይ ሆነን ችግሮቻችንን ለመፍታት በብርቱ እንስራ፤ መፍትሔም እናምጣ፤ መሳሪያ ኣንሥታችሁ እርስ በርስ በመገዳደል የምትገኙ ወገኖቻችን እባካችሁ ቆም ብላችሁ ኣስቡና ሰላምና ዳቦ ኣጥቶ ለተቸገረው ሕዝባችሁ ስትሉ ለሰላማዊ መፍትሔ ዕድል ስጡ፤
ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆኗን በትክክል የሚያረጋግጥ ሰላማዊ መፍትሔ በማስቀመጥ ለአንድነትዋና ለዕድገትዋ አጥብቃችሁ ጣሩ፤ ግጭትና መለያየት ከሚያጠፋን በቀር ምንም ዓይነት ጥቅም ሊሰጠን እንደማይችል ብዙ ማብራሪያ የሚያስፈልገው ኣይደለም፤ ስለሆነም ገዳዩን መሳሪያ ኣስቀምጡና በሃይማኖት፣ በኣንድነት፣ በስምምነትና በጭንቅላት ኃይል ሰላምን ኣምጡ፤ ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ጥሪ ነው።