ትንሣኤውን እንድታይ የተመረጠችው ማርያም:- ባለሽቶዋ ማርያም

11 Hrs Ago 216
ትንሣኤውን እንድታይ የተመረጠችው ማርያም:- ባለሽቶዋ ማርያም

አጋንንት የሰፈሩባት በዝሙትም የምትታወቅ ሰዎች የናቋት ኃጢአተኛ ነበረች፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ኃጢአቷን ፍቆላት ከቅዱሳን መካከል ደመራት፡፡ ኃጢአተኞችን አይንቅም የሚለውን ስትሰማ ሳታመነታ ወደሱ ገስግሳ ስርዬትን ያገኘች፣ በመጨረሻም ሥራዋ በዓለም ሁሉ እንዲነገር ትዕዛዝ የተሰጠላት ነች፡፡ ከዚህ ሁሉ ውርደት ያዳናት ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ እጅ ተይዞ በመስቀል ተሰቅሎ ሥጋው ወደ መቃብር በወረደ ጊዜ ትንሣኤውን እስክታይ እንቅልፍ አጥታለች፡፡ በእኩለ ሌሊትም ወደ መቃብሩ ሥፍራ ሄዳ ትንሣኤውን አይታ ለሐዋርያት አብስራለች፡፡

ወንጌላውያን መግደላዊት ማርያም እያሉ ይጠሯታል:: ለምን እንዲህ ብለው ጠሯት ቢሉ በአንድ በኩል በዘመኑ ማርያም የሚባሉ ብዙ ሴቶች ነበሩና ከእነሱ ለመለየት ሲሆን፣ በሌላ በኩል የትውልድ ቦታዋ ከእሥራኤል አውራጃዎች አንዱ በሆነው መግደሎን በመሆኑ ነው ይባላል::

ማርያም መግደላዊት ይህ ቀረሽ የማይሏት ቆንጆ ነበረችና ሰዎች ያደንቁዋት፣ ወንዶች ይከተሏት እንደነበርና አጋንንት ተጠግተው ዝሙት ያሠሯት እንደነበር ይነገራል:: በዚህም ምክንያት እጅግ ውድ ጌጦችን እና ሸቶዎችን ትወድድ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ደግሞ በእስራኤል ሕግ ዘማዊት ሴት በድንጋይ ተወግራ ትገደል ስለነበር ተደብቃ ትኖር ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዕለቱ በሚነበበው ስንክሳር ላይ የዕረፍቷ ቀኗ በሆነው የካቲት 6 እንደተመዘገበው "ማርያም ቀደም ሲል ኑሮዋን በዝሙት ያሳለፈች ሴት ነበረች፡፡ ጎልማሶችንም ትማርክ የነበረው በጌጥ እየትሸለመችም ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ወደተለመደው ተግባሯ ለመሄድ ተሸልማ አጌጠች፤ ሽቶም ተቀባች፡፡ ፊቷን በመስታወት በማየት ለአንድ ሰዓት ያህል የጉንጯ ቅላት እና ደም ግባት፤ የዓይኗ ወገግታ እና ጥራት ማማሩን በማየት አደነቀች፡፡ በዚህ ቅጽበት ግን በጎ ሀሳብ በአእምሮዋ መጣ፤ ያም ሞትንና ዓለምን ማሸነፍ ነበር" ይላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን እንደሚቀበል እና ኃጢአትን እንደሚያስተሰርይ ሲወራ በሰማች ጊዜ ገንዘቧን ሰብስባ የአልባስትሮን ሽቱ ገዝታ እሱ ወዳለበት ስምዖን ቤት እንደሄደች በሉቃስ ወንጌል ላይ ተመዝግቧል፡፡

ከአጠገቡ ስትደርስም ከእግሩ በታች ከሰገደች በኋላ በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፤ በራስ ጠጉሯም ታብሰው፣ እግሩንም ትስመው፣ ሽቶም ትቀባው እንደነበር በዚሁ ወንጌል ሰፍሯል፡፡ ኢየሱስም ለስምዖን እንዲህ አለው፤ "ይህችን ሴት ታያታለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ÷ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብክልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች፤ በጠጉርዋ አበሰች፡፡ አንተ አልሳምከኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም፡፡ አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች፡፤ ስለዚህ እልሃለሁ ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል" አለው፡፡ ወንጌልም በሚሰበክበት ሁሉም ይህ ያደረገችውን መልካም ሥራዋ እንዲነገር አዘዘ፡፡

ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት (ቅዱሳን ሴቶች) አንዷ ትሆን ዘንድም መረጣት:: ማርያም መቅደላዊት ከዚህች ቀን ጀምሮ ፍጹም ተቀየረች:: እስከ ዕለተ ሕማሙ እና ሞቱ ድረስ ተከትላ ከሁሉም ቀድማ ትንሣኤውን አየችው፡፡ በተለይም የመከራ ቀን በነበረችው ዕለተ ዐርብም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ከጐኑ ነበረች:: ከግርፋቱ እስከ ስቅላቱ እያለቀሰች ተከትላዋለች:: በእግረ መስቀሉ ያለቅሱ ከነበሩ ቅዱሳት አንስትም አንዷ እርሷ ነበረች:: ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ሲቀብሩም ከእህቶቿ ጋር አብራ ተከትላ አይታለች::

መቃብሩን ያየችው ማርያም እሁድ በሌሊት መቃብሩን ታይ ዘንድ ሽቶም ልትቀባ ገሠገሠች:: ከምን እንዳስወጣት ታውቃለችና ግርማ ሌሊቱን እና የአይሁድ ጭፍሮችን አልፈራችም:: ፍጹም ፍቅሯን እና የልቧን ንጽህና ያወቀው ክርስቶስም ከእናቱ ማርያም ቀጥሎ ከፍጥረት ወገን ትንሣኤውን ያየች የመጀመሪያዋ ሰው ትሆን ዘንድ አደላት::

በአራቱ ወንጌላት እንደተጻፈው መቃብር ባዶ ሆኖ በመቃብሩ ራስጌ እና ግርጌም ሁለት መላእክትን ተመለከተች:: ዘወር ስትል ደግሞ አንድ ሰው አየች ያየችው ከሞት የተነሳው ክርስቶስ እንደሆነ አላወቀችውምና የአትክልት ስፍራው ጠባቂ መስሏት "ጌታዬን አንተ ወስደኸው እንደሆነ ሽቶ ልቀባው ስጠኝ" አለችው እርሱም "ማርያም" አላት "ረቡኒ" አለች መምህር ሆይ ማለቷ ነው::

ኢየሱስም "ሄደሽ ለደቀ መዛሙርቴ መነሳቴን ንገሪያቸው" ብሎ የትንሣኤው አብሳሪ አደረጋት:: እሷም ሮጣ በመመለስ ለሐዋርያት ጌታዋን ማግኘቷን እርሱም መነሣቱን ነገረቻቸው:: ከትንሣኤ በኋላ ለ40 ቀናት ከእርሱ ስትማር ቆይታለች:: በ40ኛው ቀን ሲያርግም  ከሌሎቹ 120 ቤተሰብ ጋር ተባርካለች፡፡ በበዓለ ሃምሳ ከቅዱስ መንፈሱ ጸጋ ተካፍላለች:: ከዚያም በኋላ የሐዋርያትን የፍቅር ማዕድ (አጋፔ) ስታዘጋጅ እንደነበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ይናገራሉ፡፡ @መልካም በዓል@ 

ለሚ ታደሰ 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top