ረቡዕ ሦስተኛዋ የሰሙነ ሕማማት ዕለት ነች። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት በዚህ ቀን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕማማት የሚገልጹ የተለያዩ የመጽሐፍት ታሪኮች ይነገራሉ።
የዕለቱን ታሪኮች የሚገልጹ ክፍሎች ከመጽሐፍ ቅዱስ እና ከድርሳናት ይነበባሉ። ምዕመናንም በቤተክርስቲያን ተገኝተው ሕማማቱን እያሰቡ በጾም፣ በጸሎት ሆነው ይሰግዳሉ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተገለጸው ረቡዕ ዕለት የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ተከስተዋል፡-
- የካህናት አለቆች፣ የሕዝብ ሽማግሌዎች እና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ተማክረዋል።
- አንዲት በኃጢአቷ ምክንያት የተፀፀተች ሴት በስምዖን ቤት ኢየሱስ ክርስቶስን ሽቶ ቀብታዋለች።
- ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያን እና ከካህናት አለቆች ዘንድ ሠላሳ ብር ለመቀበል ተስማምቷል።
የካህናት አለቆች እና የሕዝብ ሹማምት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ይሙት በቃ ለመወሰን የሰበሰቡት ሸንጎ "ሲኒሃ ድርየም" ይባላል።
በዚህ ሸንጎ ላይ በአብዛኛው የተሰየሙት ሰዱቃውያን ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ነበሩ። ሸንጎው በአጠቃላይ ሰባ ሁለት አባላት የነበሩት ሲሆን የሚመራውም በሊቀ ካህናቱ በቀያፋ ነበር።
በዕለቱ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ይዘው እንደሚገድሉት አይሁድ በዚህ ሸንጎ መክረዋል። ይሁዳም ጸሐፍት ፈሪሳውያን እና የካህናት አለቆች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ያውቅ ስለነበር "ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ? እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤" በማለት ኢየሱስን አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተስማምቷል።
ክርስቶስ ያስተምር በነበረበት ወቅት የአስቆሮቱ ይሁዳ ከምእመናን ለሚሰበሰበው ገንዘብ ሰብሳቢ (ዐቃቤ ንዋይ) ነበር።
ከሚሰበሰበው ሙዳየ ምጽዋት ለግል ጥቅሙ እየቀረጠ የማስቀረት የእጅ አመል ነበረበት። ይሁዳ ፍቅረ ንዋይ እንደሚያጠቃው ድብቅ አመሉ ጎልቶ የወጣው ኢየሱስ ክርስቶስ በስምዖን ቤት ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ በቀባችው ጊዜ ነው ይላሉ የቤተክርስቲያን አባቶች። ለዚህም የሚጠቅሱት በዚያች ዕለት ይሁዳ የተቃውሞ ድምፅ ያሰማ በመሆኑን ነው።
ይሁዳ "ይህ ሽቱ ተሽጦ ለድሆች ቢሰጥ መልካም ነበር፤" በማለት ሀሳብ አቅርቦ ነበር። ይሁዳ ይህን ያለው ሽቶው ቢሸጥ የሚያገኘውን አሥር በመቶ ለእርሱ ስለሚሆን፣ ሽቶው በኢየሱስ ክርስቶስ እግር ላይ ከፈሰሰ የሚተርፈው ስለማይኖር እንደሆነ ይነገራል። ይሁዳ ተቆርቋሪ መስሎ ያቀረበው ሀሳብ ተቀባይነት በማጣቱም ማኩረፊያ ያገኘ መስሎት በቀጥታ ከካህናት አለቆች ዘንድ ሔዶ ጌታን በሠላሳ ብር ለመሸጥ ተዋዋለ። ይህ ሰላሳ ብር 300 ዲናር የሚያወጣው ሽቶ ቢሸጥ ያገኝ የነበረው ገንዘብ መጠን እንደነበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ያስተምራሉ። ይህ ታሪክም በማቲዎስ፣ በማርቆስ እና በሉቃስ ወንጌላት ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል።
የአስቆሮቱ ይሁዳ ከአሥራ ሁለቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አንዱ ስለነበር እንደ ሌሎች ሐዋርያት ከእርሱ ተምሯል። በረከተ ኅብስቱን ተመግቧል። ልዩ ልዩ ተአምራት በኢየሱስ ክርስቶስ እጅ ሲደረጉ ሁሉ ተመልክቷል። ክርስቶስም ከሌሎች ሐዋርያት ሳይለየው እግሩን አጥቦታል። ይሁዳ ግን ለሐዋርያነት የጠራውን፣ ተንበርክኮ እግሩን ያጠበውን ጌታውን ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል። ይህ ታሪክም፣ "የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሔዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት!" ተብሎ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 26 ቁጥር 24 ተጽፏል።
የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች እንደሚያስተምሩት ሌሎች ሐዋርያት ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ፍቅሩን ገንዘብ ሲያደርጉ ገንዘብን የመረጠው ይሁዳ ግን እርግማንን ነው ያተረፈው። "ገንዘብ የኃጢአት ሥር ነው፤" ተብሎ አንደ ተነገረ የኃጢአት ሥር የተባለው ገንዘብ የክርስቲያኖችን ሕይወት ያዳክማል እና ምእመናን እንደ ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር እንዳይወድቁ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ይላሉ። "ሰው ይህን ዓለም ቢያተርፍ ነፍሱን ከጎዳ ምን ይጠቅመዋል?" ተብሎ የተነገረውን ቃል ልብ ማለት ጠቃሚ እንደሆነም ይመክራሉ።
ክርስቲያን ነን በማለት የክርስትናውን ስም በመያዝ እምነታቸውን፣ የቆሙበትን ዓላማ በመገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ዛሬም እንደ ይሁዳ ክርስቶስን እየሸጡት እንደሆነ ሊገነዘቡት እንደሚገባም ያወሳሉ። ለድሆች መመጽወት ክርስቲያናዊ ግዴታ ቢሆንም፣ በድሆች ስም የሰውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው።
እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ድሆችን ለረኃብ ለችግር ባልንጀራቸውን ለመከራ እና ለሞት አሳልፈው ሲሰጡ ምንም አይጸጽታቸውም። እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ሕይወታቸውን ለገንዘብ ፍቅር ሳይሆን ለእምነታቸው እና ለባልንጀራቸውን አሳልፈው መስጠት ይኖርባቸዋል ይላሉ አባቶች። ክርስቲያኖች በፍቅረ ንዋይ ተጠምደው ሰዎችን አሳልፎ በመስጠት ለአይሁዳዊ ሸንጎ ምቹ ሆነው መገኘት እንደሌለባቸው መገንዘብ አለባቸውም ይላሉ።
በለሚ ታደሰ