"ኦፕሬሽን ስፓይደርስ ዌብ" ወይም "የሸረሪት ድር ዘመቻ" የሩሲያን ግዛት በጥልቀት በመዝለቅ በዩክሬን የተፈጸመ የተቀናጀ የድሮን ጥቃት ነው።
በጥቃቱ በአምስት የጦር አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ የነበሩ እጅግ ዘመናዊ የሩሲያ ቦምብ ጣይና የክትትል አውሮፕላኖችን ወድመዋል።
ዘመቻው በፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ክትትል የተደረገበት እንደነበር የዩክሬን የደህንነት አገልግሎት (SBU) ገልጿል።

ጥቃቶቹ እንዴት ተፈጸሙ?
ፕሬዚደንት ዘለንስኪ "ይህ ተልዕኮ ከዕቅድ አንስቶ እስከ ውጤታማ አፈጻጸም ድረስ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ከዘጠኝ ቀናት የፈጀ ነው" ሲሉ በኤክስ የማኅበራዊ ትስስር ገጻችው ላይ አስፍረዋል።
ዩክሬን ጥቃቱን ለማቀነባበር በከባድ መኪናዎች ላይ በተገጠሙ የእንጨት ሳጥኖች (ካቢኖች) ውስጥ የተደበቁ ትናንሽ ድሮኖችን ተጠቅማለች።
ከባድ መኪናዎቹ ኢላማቸው ጋር ሲደርሱ፣ ጣሪያዎቹ በርቀት መቆጣጠሪያ አማካኝነት ተከፍተው ድሮኖቹ እንዲበሩ መደረጉን በርካታ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ ቪዲዮዎች ድሮኖቹ ከቆሙ ከባድ መኪናዎች ላይ ሲነሱና በአውሮፕላን ማኮብኮቢያዎች ላይ የነበሩ ትላልቅ አውሮፕላኖችን ሲመቱ ያሳያሉ።

በዘመቻው 117 ድሮኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን፤40 የሩሲያ አውሮፕላኖች መመታታቸውን እና 7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የንብረት ውድመት በሩሲያ ላይ መድረሱን ዩክሬን አስታውቃለች።
ይሁንና የዩክሬን የዘርፉ ኤክስፐርቶች ውድመቱ 2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን መናገራቸውን ቢቢሲ እና ፎክ ኒውስ ዘግበዋል።
ፕሬዚደንት ዘለንስኪ ዘመቻውን በማዘጋጀት ላይ የተሳተፉ አካላት ከሩሲያ ግዛት በወቅቱ እንዲወጡ መደረጉን ገልፀው፤ የደህንነት አገልግሎት መሪ የሆኑትን ጄነራል ቫሲል ማሊዩክን አመስግነዋል።
በተጨማሪም የጥቃቱ አንዳንድ ዝርዝሮች ገና ይፋ ሊደረጉ እንደማይችሉ ጠቁመው፤ ነገር ግን "የዩክሬን እርምጃ ያለጥርጥር በታሪክ መዛግብት ውስጥ የሚሰፍር ነው" ብለዋል።

የሞስኮ ምላሽ
ሩሲያ ጥቃቱን "የሽብር ድርጊት" ብላዋለች። ሆኖም ኃይሎቿ ጥቃቱን እንደመከቱት ገልጻለች።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በሙርማንስክ፣ ኢርኩትስክ፣ ኢቫኖቮ፣ ራያዛን እና አሙር በተባሉ አምስት ግዛቶች በሚገኙ የአየር ማረፊያዎች ላይ ጥቃት እንደተፈጸመ አረጋግጧል።
በጥቃቱ በርካታ አውሮፕላኖች በእሳት እንደተያያዙም ጠቁመዋል። የሩሲያ ባለሥልጣናት አንዳንድ ተጠርጣሪዎች መታሰራቸውን እንደተናገሩ ፎክስ ኒውስ አስነብቧል።
አንዳንድ ሩሲያውያንም ሀገራቸው የድሮን ጥቃቱን ማስቀረት ባለመቻሏ እየተቹና፤ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸው ባለስልጣናትን መጠየቅ እንደሚገባ ሀሳብ መሰንዘራቸውን በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ጥናት የሚያደርገው ኢንስቲትዩት ፎር ዘ ስተዲ ኦፍ ዋር ገልጿል።
የሩሲያ ዱማ ግዛት ምክትልና የቀድሞ የደቡብ ወታደራዊ ዲስትሪክት ምክትል አዛዥ የነበሩት ጡረተኛው ሌተናል ጄነራል አንድሬ ጉሩሌቭ፥ የሩሲያ ልዩ አገልግሎቶች የአየር ኃይል ሰፈሮችን በበቂ ሁኔታ ባለመጠበቃቸውና ከባድ መኪናዎቹ ወደ ዒላማዎቹ እንዲጠጉ በመፍቀዳቸው የሰላ ትችት ሰንዝረዋል።
መቋጫ ያላገኘው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በርካታ ውድመት እያስተናገደ ይገኛል። የቢቢሲ ዘገባ እንዳመላከተውም የሰሞኑ ጥቃት በቱርክ ሊከናወን በታቀደው ሁለተኛ ዙር የሰላም ድርድር ላይ መጥፎ ጥላ እንዳያጠላ ተሰግቷል።
በጌትነት ተስፋማርያም