የሳይበር መጭበርበር ቢያጋጥምዎ ከኢመደአ ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉ ያውቃሉ?

11 Hrs Ago 92
የሳይበር መጭበርበር ቢያጋጥምዎ ከኢመደአ ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉ ያውቃሉ?

የቴክኖሎጂ መራቀቅን ተከትሎ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሳይበር ጥቃቶች በዓይነት እና በመጠን እየተስፋፉ ለተቋማት እንዲሁም ለግለሰቦች ተግዳሮት እየሆኑ መጥተዋል።

በዚሁ የሳይበር ጥቃት ብዙዎች የመረጃ መመንተፍ፣ የገንዘብ መጭበርበር እንዲሁም የማኅበራዊ ሕይወት መቃወስ እየገጠማቸው ወደ አላስፈላጊ ችግሮች እየገቡ ይገኛሉ። 

ይህ የሳይበር ጥቃት እየጨመረ የመጣው ታዲያ የማኅበረሰቡ የሳይበር ደኅንነት ግንዛቤ እየተራቀቀ ከመጣው የቴክኖሎጂ ውጤት ጋር ባለመጣጣሙ እንደሆነ ይነሣል።

በተለያዩ የማጭበርበሪያ ዘዴዎች የሳይበር ጥቃት ደርሶብናል የሚሉ በርካቶችም በኢቢሲ ዶትስትሪም አማራጮች በውስጥ መስመር መረጃዎችን እየላኩልን ይገኛሉ። 

አጭበርባሪዎቹ የተለያዩ ማኅበራዊ ትሥሥር ገጾችን በመጠቀም “በቀን ይህን ያክል ብር ይሥሩ” በሚል የማታለያ ማስታወቂያ ሊንኮችን ለተገልጋዮች ይልካሉ። 

በእንደዚህ ዓይነት የሳይበር ጥቃት ገንዘቡን የተጭበረበረው ሱራፌል፣ "በማኅበራዊ የትሥሥር ገጾች የሥራ ማስታወቂያ ተብለው በተለጠፉ ሊንኮች አማካኝነት ‘በቀን ከ10 ሺህ ብር በላይ ይሥሩ’ በሚል በዋትሳፕ ካወሩኝ በኋላ ወደ ቴሌግራም ገባሁ፣ ሊንክ ልከውልኝ በዚያው ሊንክ ከተመዘገብኩ በኋላ ለአመኔታ ትንሽ ብር ከፍለውኝ ቀጥለውም ብዙ ብር ወስደውብኝ አድራሻቸውን አጠፉብ" ሲል ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግሯል።

እነዚህ ሰዎች የውጭ ሀገር ስልክ በመጠቀም እንዳጭበረበሩት የጠቀሰው ሱራፌል፣ ባንክ ሄዶ ቢጠይቅም ብሩ የተወሰደው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ስለሆነ ምንም ማድረግ እንዳልተቻለ ገልጿል።

በተመሳሳይ የሳይበር ጥቃት የደረሰባት ናኒ በተጠለፈ የጓደኛዋ ፌስ ቡክ አካውንት ጓደኛዋን መስለው በመግባት፣ "አዲስ የጀመርኩት የኦላይን ሥራ ስላለ አባል ላድርግሽ በሚል" አውርተዋት የሷንም አካውንት በቁጥጥራቸው ስር አድርገው እሷን መስለው ወዳጅ ዘመድዎችዋ ጭምር ጋር እየደወሉ ገንዘብ እንደተቀበሉ እና አሁንም እየተቀበሉ እንደሆነ ተናግራለች። 

ኢቢሲ ዶትስትሪም ይህንኑ መነሻ በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት? ሲል የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት የተቀናጀ የሳይበር መከላከል አገልግሎት ዲቪዥን ኃላፊ የሆኑትን አቤል ተመስገንን ጠይቋል።

ማኅበረሰቡ ስለሚጠቀመው የማኅበራዊ ትሥሥር ገጾች ባህሪ ማወቅ እና ማንኛውም የቅርብ ሰው እህት፣ ወንድም፣ ዘመድ፣ ጓደኛ ምንም አይነት ሊንክ ቢልኩልን ሊንኩን ከመክፈታችን በፊት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ እና እነዚህ ሊንኮች ወዲያው ከስልካችን ማጥፋት እንደሚገባ ገልጸዋል። 

የሳይበር ደኅንነት ግንዛቤየችንን ማሳደግ አለብን ያሉት ኃላፊው፣ የምንጠቀማቸውን መተግበሪያዎች ጠንካራ የይለፍ ቃል በፊደላት በቁጥር እንዲሁም በተለያዩ ምልክቶች የተዋቀረ የይለፍ ቃል መጠቀም፣ ለተለያዩ አካውንቶች አንድ ዓይነት የይለፍ ቃል አለመጠቀም፣ ባለሁለት ወገን ደረጃ ማረጋጋጫ መጠቀም እና መተግበሪያው ያስቀመጠውን የደኅንነት መጠበቂያ ዘዴዎችን መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።

የማኅበራዊ ትሥሥር ገጾች የማንነት ስርቆት ጋር በተያያዘ ከሜታ ግሩፕ ጋር በቅርበት እየሠሩ እንደሆነ ገልጸው፣ ማኅበረሰቡ ለሚደርስበት መጭበርበርም ሆነ የማንነት ስርቆት በፍጥነት ለተቋሙ ጥቆማ ቢያደርግ የመመለስ ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ ተናግረዋል።

ማኅበራዊ የትሥሥር ገጾቻችን ከኛ ቁጥጥር ውጪ እንደሆኑ ስናውቅ በአካባቢያችን ለሚገኙ ቤተሰብ፣ የሥራ ባልደረባ፣ ጓደኛ፣ በፍጥነት መናገር እና የምንጠቀማቸውን ከባንክ ጋር የተያያዙ መተግበሪያዎች ደኅንነት ወደ ባንክ በመሔድ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ እና ማኅበረሰቡ እንዲጠነቀቅ መክረዋል። 

በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ‘ኢትዮ-ሰርት’ የሚባል ቡድን የተቋቋመ ሲሆን፣ የሀገራችንን የሳይበር ምኅዳር ደኅንነት የሚጠብቅ በግለሰብ እና ተቋም ላይ ጥቃት ቢፈፀም የሚመዘግብ፣ ትንተና የሚሰጥ እና መፍትሔ የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸዋል። 

ማንኛውም አካል የትኛውም ዓይነት የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ቢደርስበት ወዲያውኑ ለ‘ኢትዮ-ሰርት’ በነፃ የስልክ መስመር 933 ጥቆማ ቢሰጡ ያሉበት ድረስ በመሔድ ሁኔታውን በመተንተን ወደነበረበት የመመለስ ሥራ ይሠራል  ብለዋል። 

በሔለን ተስፋዬ

#EBC #ebcdotsream #cybersecurity #fraud


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top