ሰውነትን ያስቀደሙ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች

3 Days Ago 229
ሰውነትን ያስቀደሙ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች

መንግሥት ባለፉት በሰባት ዓመታት በርካታ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ እጅግ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ታዲያ በቀጥታ ከሕዝብ ጋር የሚገናኙ እና ችግር ፈቺ መሆናቸው በጊዜ ሒደት የታየ ጉዳይ ነው።

ባለፉት ሰባት ዓመታት በበጎ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል አንዱ ሰው ተኮር ሥራ “ለነገዋ” የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ነው።

ይህ ማዕከል ለሴቶች መለወጥ መሠረት የሚጥል ማዕከል ሆኖ ከተመሠረተ በኋላ በርካታ ሴቶችን ከጎዳና በማንሳት እና ከሱስ በማላቀቅ በተለያዩ ሙያዎች ተሰማርተው ራሳቸውን እና ማኅበረሰባቸውን የሚጠቅሙ ዜጋ ሆነው እንዲገኙ ማድረግ የቻለ ተቋም ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የማዕከሉ የምረቃ መርሐ-ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ “በአዲስ አበባ ከተገነቡ ፕሮጀክቶች ሁሉ ይህ ማዕከል ድንቅ የሆነ ሥራ ነው” ሲሉ ነበር የገለጹት።

ማዕከሉ እንደሀገር ያሉብንን ስብራት ለመሻገር ከሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ተግባር መሆኑን እና አርቆ የማሰብ እና የመስከን ውጤት መሆኑንም መስክረውለታል።

ማዕከሉ ሴቶች ቀጣይ ተስፋቸውን በማለምለም ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚሸጋገሩበት የክህሎት ማበልፀጊያ ከመሆኑም ባሻገር ከችግሮቻቸው ተላቅቀው ለነገ ሕይወታቸው መሠረት የጣለም ጭምር ነው።

በሌላ በኩል በበጎ ፍቃድ ፕሮግራም ቀና ልብ ያላቸው በጎ ፍቃደኛ ባለሀብቶችን በማስተባበር በተለያዩ አካባቢዎች በተከናወኑ ሰው ተኮር ሥራዎች አቅመ ደካሞች አረጋውያን እና የሀገር ባለውለታዎች መጠለያ እንዲያገኙ መደረጉ ነው።

በተለይም በየሙያ ዘርፋቸው ሀገራቸውን ያገለገሉ ባለውለታዎች በማምሻው የዕድሜ ዘመናቸው ክብር አግኝተው እንዲኖሩ ከማድረግ ረገድ በሰው ተኮር ፕሮጀክቶች የተሠሩ ሥራዎች አመርቂ ናቸው።

በአስከፊ የአኗኗር ሁኔታዎች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ አካል ጉዳተኞች እና አቅመ ደካማ አረጋውያንን ጨምሮ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከ160 ሺህ በላይ ለሆኑ ቤተሰቦች በዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ሆነዋል።

ሌላኛው ሰው ተኮር ፕሮጀክት የ90 ቀናት ፕሮጀክት ሲሆን በዚህም ጣሪያ እና ግድግዳው በፈራረሰ ቤት ውስጥ ፀሐይ እና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው ይኖሩ ለነበሩ ግለሰቦች የሰውነት ክብራቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ለማስቻል ቤቶቻቸውን የማደስ እና አዲስ ቤት ገንብቶ የመስጠት ሥራዎች ተሠርተዋል።

የተማሪዎች ምገባ ማዕከላትም፣ በአቅም ማነስ ምክንያት ቁርሳቸውን እንክ ሳይበሉ ትምህርት ቤት ለመሔድ ይገደዱ የነበሩ ተማሪዎች በትምህርት ቤቶቻቸው እንዲመገቡ ዕድል የሰጡ ናቸው።

በዚህም ትውልዱ ትምህርቱ ላይ እንዲያተኩር በማስቻል ለመፃኢ ጊዜ ምርታማ ዜጋ እንዲፈጠር መሠረት ተጥሏል።

የመንገድ ዳርቻ ማስዋብ ሥራ፤ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል የእንጀራ እና የዳቦ ፋብሪካዎች መቋቋማቸው ለበርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማገዝ ተችሏል።

በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የተሠሩ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች የዜጎችን ጊዜያዊ ችግሮች እና ፈታኝ ወቅቶች እንዲሻገሩ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በዘለቄታዊነት ችግር ፈቺ መሆናቸውም በተግባር የተመሰከረ ነው።

ሌላኛው ሰው ተኮር ፕሮጀክት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች የተዘጋጁ የምገባ ማዕከላት ናቸው።

የኑሮ ጫና ያለባቸው እና በምግብ እጦት የተጎዱ ወገኖች በእነዚህ የምገባ ማዕከላት ዕለታዊ ጉርሳቸውን ማግኘት ችለዋል።

ማዕከላቱ ለእጅ አጠር ወገኖች በየቀኑ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት መመገብ በመቻላቸው በዚህ ረገድ ስኬታማ የሆነ ሥራ መሥራት ተችሏል።

ይህ ተግባር በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነት በማግኘት ሽልማት እስከማግኘት የደረሰ ሲሆን ለበርካታ ሀገራትም ልምድ ለማካፈል የተቻለበት በጎ ተግባር መሆኑ ተመስክሮለታል።

ሰው ተኮር የሆኑ ሥራዎች ‘ከሰው፣ በሰው፣ ለሰው’ መሠረታቸው ሰውኛ የሆኑ ስሜቶች በመሆናቸው ተግባራዊ ሲደረጉም የማኅበረሰቡን ችግር መሠረት ያደረጉ ሆነው በቀጥታ የመፍትሔ ሐሳብ ይዘው ነው የሚመጡት።

ሰው ተኮር ተግባራቱ ቅድሚያ ለሰው ክብር እና ፍቅር በመስጠት ብልፅግናን ለሀገራችን የሚያጎናፅፉ መሆናቸውም የተረጋገጠ ነው።

በኔፍታሌም እንግዳወርቅ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top