ከ338 ሚሊዮን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች ተያዙ

4 Days Ago 262
ከ338 ሚሊዮን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች ተያዙ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ብሔራዊ ኢንተርፖል፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን በጋራ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከ338 ሚሊዮን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች መያዛቸውን አስታውቀዋል።
 
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም ወልዴ፤ በሕገ ወጥ የመድኃኒት ዝውውር ላይ ተሰማርተው ህብረተሰቡን ለከፋ የጤና ችግር እየዳረጉ ያሉ አካላትን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል።
 
በቁጥጥር ሥር የዋሉት መድኃኒቶች የወባ፣ የካንሰር፣ ከመንግስት ተቋማት ተሰርቀው የወጡ የፕሮግራም መድኃኒቶች እና ጥቅም ላይ የማይውሉ የሕክምና መሳሪያዎች ጭምር እንደሚገኙበት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
 
የጉሙሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እዘዘው ጫኔ በበኩላቸው፤ የጤና አገልግሎትን በጥራትና በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ሰሞኑን በአዲስ አበባና በአዳማ ከተማ ሕገ-ወጥ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመግታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ኦፕሬሽን መደረጉን ጠቅሰው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
 
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የብሔራዊ ኢንተርፖል ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችና ኦፕሬሽን ዋና ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጥሩወርቅ መንግስቴ በበኩላቸው፤ ሐሰተኛ፣ ሕገወጥ መድሃኒቶች እና የሕክምና መሣሪያዎችን ለመቆጣጠር ፖንጂያ የተሰኘው ዓመታዊ የኢንተርፖል ኦፕሬሽን መካሄዱን ጠቁመዋል።
 
በዚህም በአዲስ አበባ እና በአዳማ ከተማ በተመረጡ 23 የተለያዩ ቦታዎች የተለያዩ መድኃኒቶችን በመኖሪያ ቤት፣ በመጋዘን እና በኮንቴነር አከማችተው የተገኙ 19 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
 
ኅብረተሰቡ አጠራጣሪ የመድኃኒት ክምችት እና የአገልግሎት ጊዜው ያለፋባቸው መድኃኒቶችን ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኝ የፀጥታ አካላት ማሳወቅ እንደሚገባው ዋና ኢንስፔክተር ጥሩወርቅ መንግስቴ ማሳሰባቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል።
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top