አሜሪካ በዓለም ላይ ከፍተኛው የብሔራዊ ዕዳ መጠን ያላት ሀገር ነች። የአሜሪካ ያለባት ዕዳ 36.2 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል። ይህም ከአሜሪካ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) አንፃር 122 በመቶ ሆኗል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ዕዳ በየሦስት ወሩ በ1 ትሪሊዮን ዶላር ይጨምራል።
ከ36.2 ትሪሊዮን ዶላሩ የአሜሪካ ዕዳ ውስጥ ሦስት አራተኛው ከሀገር ውስጥ የቀረበ ሲሆን፤ ከአሜሪካ የግል ባለሀብቶችና ተቋማት፣ ከአሜሪካ መንግስት ኤጀንሲዎች እንዲሁም ከፌደራል መጠባበቂያ የመጣ ነው።
ከግለሰቦች መካከል ዋረን በፌት፣ በኩባንያቸው በርክሻየር ሃዛዌይ አማካኝነት፣ የ314 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሰነዶችን በመያዝ መንግሥታዊ ያልሆነ ብቸኛው ትልቁ ግምጃ ቤት ሰነዶችን የያዙ ባለሃብት መሆናቸውን አልጃዚራ ዘግቧል።
አሜሪካ ካለባት አጠቃላይ ብድር ውስጥ አንድ አራተኛውን የያዙት ደግሞ የውጭ ሀገራት ባለሀብቶች ናቸው።
ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ በውጭ ሀገራት ባለሃብቶች የተያዘው የአሜሪካ ዕዳ ድርሻ በአምስት እጥፍ ጨምሯል። እ.አ.አ. በ1970 በውጭ ሀገር ባለሀብቶች የተያዘው የብድር አቅርቦት 5 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ይህ አኃዝ ወደ 25 በመቶ ከፍ ብሏል።
የውጭ ባለሀብቶችና ተቋማት ከአሜሪካ የግምጃ ቤት የገዙት የ9.05 ትሪሊዮን ዶላር ሰነድ አላቸው። ከዚህም ውስጥ የጃፓን 1.13 ትሪሊዮን ዶላር፣ የዩናይትድ ኪንግደም 779.3 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም የቻይና ባለሃብቶች 765.4 ቢሊዮን ዶላር በመያዝ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
ትራምፕ በተለያዩ ሀገራት ላይ ለጣሉት የቀረጥ ዕርምጃ ምላሽ፣ ጃፓንና ቻይናም ያላቸውን ከፍተኛ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሰነዶች ክምችት ለመደራደሪያነት እንደሚጠቀሙበት አመልክተዋል።
የአሜሪካ ዕዳና ኮንግረሱ
መንግሥት በየዓመቱ ከሚሰበስበው ገቢ በላይ ወጪ ሲያወጣ የበጀት ጉድለት ይከሰታል። ጉድለቱን ለመሸፈን ደግሞ ብድር ስለሚወስድ የዕዳ መጠኑ እያደገ ይገኛል።
አሜሪካ ብድረ በሕግ አውጪው አካል ይሁንታ እንዲያገኝ ለማድረግ ደግሞ የአሜሪካ ኮንግረስን ገደብን መከተል ይኖርባታል። ኮንግረሱ የአሜሪካን መንግስት እንደ ሶሻል ሴኩሪቲ፣ የጤና እንክብካቤ እና መከላከያ ያሉ ነባር ግዴታዎችን ሸፍኖ መስራት እንዲችል ምን ያህል ገንዘብ መበደር እንደሚችል ገደብ ያስቀምጣል።
ይህ ገደብ "የዕዳ ጣሪያ" በመባል ይታወቃል። ጣሪያው ላይ ሲደረስ፣ ኮንግረሱ ገደቡን ካላነሳው ወይም ለጊዜው ካላገደው በስተቀር መንግሥት ተጨማሪ መበደር አይችልም።
ከ1960 ጀምሮ ኮንግረሱ የዕዳ ጣሪያውን 78 ጊዜ አሻሽሏል፤ ይህም አሜሪካ ተጨማሪ ገንዘብ እንድትበደር አስችሏታል።
ለብድሩ የግምጃ ቤት ሰነዶች ጠቀሜታ
አሜሪካ ገንዘብ መበደር ስትፈልግ የምታማትረው የፌደራል መንግሥቱ የገንዘብ (ፋይናንስ) ጉዳዮች መምሪያ ወደ ሆነው ግምጃ ቤት (Treasury) ነው።
ገንዘብ ለመበደር፣ ግምጃ ቤቱ የተለያዩ የሰነደ ሙዓለ ንዋኖችን ወስዶ ለባለሀብቶች ይሸጣል።
እነዚህ የዕዳ ሰነዶች በመሠረቱ ባለሀብቶች ለአሜሪካ መንግሥት የሚያበድሩት ገንዘብ ሲሆን፣ መንግሥትም ከወለድ ጋር መልሶ ለመክፈል ቃል ይገባል።
የተለያዩ የዕዳ ሰነዶች በተለያየ ጊዜ ለባለሃብቶቹ የሚከፈሉበት ጊዜ አላቸው።
ለመንግስት ብድር የሚያስፈልጉ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ (ግምጃ ቤት ሰነድ) አይነቶች
- የአጭር ጊዜ የግምጃ ቤት ሰነዶች (T-bills) የአጭር ጊዜ ሲሆኑ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብድሩ ከነወለዱ የሚከፈልባቸው የግምጃ ቤት ሰነዶች ናቸው።
- የመካከለኛ ጊዜ የግምጃ ቤት ኖቶች (T-notes) ከ2 እስከ 10 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ብድሩ ከነወለዱ የሚከፈልባቸው የግምጃ ቤት ሰነዶች ናቸው።
- የረጅም ጊዜ የግምጃ ቤት ቦንዶች (T-bonds) ከ20 እስከ 30 ዓመታት ውስጥ የብድር ክፍያቸው የሚጠናቀቅና በየ6 ወሩ የወለድ ክፍያቸው ይፈጸማል።
መንግሥት ተጨማሪ ገቢ ለማግኘትና ብሔራዊ ዕዳውን ለመክፈል ግብር ሊጨምር ይችላል፤ ይህም ሕዝቡ ላይ ወጪን ይጨምራል።
እየጨመረ የሚሄድ ዕዳ ለከፍተኛ የወለድ ምጣኔዎች ሊዳርግ ስለሚችል፣ የቤት መግዣ ብድሮች፣ የመኪና ብድሮች እና የክሬዲት ካርድ ዕዳዎች የበለጠ ውድ እንዲሆኑ ያደርጋል።
በጌትነት ተስፋማርያም