ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በመጀመሪያው የአፍሪካ ጉብኝታቸው ወደ አንጎላ ሊያቀኑ ነው

2 Mons Ago 603
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በመጀመሪያው የአፍሪካ ጉብኝታቸው ወደ አንጎላ ሊያቀኑ ነው

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በስልጣን ዘመናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ በሚያደረጉት ጉብኝት በመጪው ሳምንት ወደ አንጎላ ሊያቀኑ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በአንጎላ የሚያደርጉት ጉብኝት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በፈረንጆቹ 2015 ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራትን ከጎበኙ በኋላ የመጀመሪያው እንደሚሆንም ተጠቅሷል።

የፕሬዝዳንቱ ጉዞ በመስከረም ወር ከሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ በኋላ እና ከህዳር 5 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት እንደሚሆን ሮይተርስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር አንጎላ በመጪው ሳምንት ያደርጉታል ስለተባለው ጉዞ ከኋይት ሃውስ የተሰጠ መግለጫ እንደሌለም ነው የተገለጸው፡፡

ጆ ባይደን በ2023 መጨረሻ ላይ አንጎላን ለመጎብኘት ተዘጋጅተው የነበረ ሲሆን፤ በጥቅምት ወር የእስራኤል-ሃማስ ጦርነት መከሰቱን ተከትሎ ጉዞው ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ዘገባው አስታውሷል።

ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ህዳር ወር የአንጎላን ፕሬዝዳንት ጆአዎ ሎሬንኮን በኋይት ሀውስ ተቀብለው ያነጋገሩ ሲሆን፤ በውይይታቸውም በአንጎላ ጉብኝት ለማድረግ ሃሳብ እንዳላቸው  አንስተው እንደነበር ተጠቁሟል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top