በኡጋንዳ የጦር ዋና አዛዥ ጄነራል ሙሆዚ ካይኔሩጋብ የተመራ ልዑክ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብቷል።
በጦር አዛዡ የተመራው ልዑክ ከኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ጋር የሁለቱ ሀገራት በመከላከያ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ መክሯል።
የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፤ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ በመከላከያ ዘርፍ የትብብር ስምምነት አንዳላቸው በመግለጽ፤ ከልዑክ ቡድኑ ጋር ትብብሩን ማጠናከር በሚቻልባቸው ዘርፎች ላይ ተወያይተናል ብለዋል።
ሀገራቱ በመከላከያ ዘርፍ በሰው ሀይል ልማት፣ በኢንዱስትሪ፣ በመረጃ ልውውጥ እንዲሁም ወንጀልን በመከላከል በጋራ ይሰራሉ ተብሏል።
የኡጋንዳ ጦር ዋና አዛዥ ጄኔራል ሙሆዚ ካይኔሪጋባ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ በመከላከያ ዘርፍ የትብብር ስምምነት እንዳላቸው በማስታወስ፤ አሁን ያደረጉት ውይይት በጣም ወሳኝ ነው ብለዋል።
በቀጣይም በየደረጃው ካሉ ኃላፊዎች ጋር ውይይት በማድረግ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ እንሰራለን ብለዋል።
በመስከረም ቸርነት