የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የመሠረቱት "የአዳም ፋውንዴሽን" የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ምሥረታውን ይፋ አድርጓል።
አቶ ደመቀ መኮንን በቦርድ ሊቀመንበርነት የሚመሩት "የአዳም ፋውንዴሽን"፤የመንግስት ባለስልጣናት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በተገኙበት ይፋዊ የማብሰሪያ ሥነ ሥርዓቱን በዛሬው ዕለት ተከናውኗል።
ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ልማትና እድገት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የገለፁት የፋውንዴሽኑ መስራች አቶ ደመቀ መኮንን፤ በተለይ ህፃናትና እናቶች ላይ በመስራት ብሎም መቀንጨርን በመዋጋት ደህንነቱ የተጠበቀ ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
"በአፍሪካ መቀንጨርን መግታት" የሚል መሪ ሀሳብ ያለው ፋውንዴሽኑ፤ ከኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የምዝገባ የምስክር ወረቀት ያገኘው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ እንደነበር ተገልጿል።
"የአዳም ፋውንዴሽን" በሥነ ምግብ ላይ መስራት ዋና ዓላማው ያደረገ ሲሆን መቀንጨርን ለመግታት የሚያስችሉ ባለብዙ ዘርፍ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ይሰራል ተብሏል።