የራሱን የሰርግ መልስ ፕሮግራም አቋርጦ የአንዲት ወላድ እናትን ሕይወት ያተረፈው ዶክተር

18 Hrs Ago 79
የራሱን የሰርግ መልስ ፕሮግራም አቋርጦ የአንዲት ወላድ እናትን ሕይወት ያተረፈው ዶክተር
የራሱን የሰርግ መልስ ፕሮግራም አቋርጦ የአንዲት ወላድ እናት እና የልጇን ሕይወት ያተረፈው ዶ/ር በየነ አበራ ከሰሞኑ የማኀበራዊ ትስስር ገጾች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
 
በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ በንግስት እሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚያገለግለው ዶ/ር በየነ አበራ፣ ከትናንት በስቲያ እሁድ የመልስ ፕሮግራሙን ከቤተ ዘመድ ጋር እያከናወነ ነበር፡፡
 
ወደ ምሽቱ 12 ሰዓት ገደማ የአንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ባለቤት ወደ ዶ/ር በየነ ስልክ አፈላልጎ ይደውላል፡፡ ሐኪሙ ሲያነሳው የተሸበረ ድምጽ "ልጄ ሊታፈን ስለሆነ ቀዶ ጥገና መደረግ አለበት ድረስልን" ይለዋል፡፡
 
ዶክተር በየነ የመልስ ፕሮግራሙን በመተው ወደ ሕክምና ተቋም በማምራት በምጥ ጭንቅ ላይ የነበረችውን ሴት በሰላም የመጀመሪያ ልጇን እንድትታቀፍ አስችሏል፡፡
 
የሆስፒታሉ የኦፕሬሽን ቴአትር ዳይሬክተር የሆነው ዶክተር በየነ፤ "የተለየ ነገር አላደረኩም ፤ ግዴታዬን ነው የተወጣሁትም" ሲል ለEBC DOTSTREAM ተናግሯል፡፡
 
"በማኀበራዊ ትስስር ገጾች የተዘዋወረው ፎቶ ጉዳዩን መነጋገሪያ አደረገው እንጂ ይሄ የዘወትር ሥራዬ ነው" ሲልም አክሏል፡፡
ሐኪሙ "የጤና ባለሙያዎች ማኀበረሰቡን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል ልናገለግለው ይገባልም" ብሏል፡፡
 
"ባለቤትህ ከመልስ ፕሮግራሙ ተነስተህ ስትሄድ ምን አለች?" ተብሎ ከEBC DOTSTREAM የተጠየቀው ዶ/ር በየነ ፤ ባለቤቱ ሙያውን አውቃ እና አምናበት በመጋባታቸው ዝግጅቱን አቋርጦ መሄድ እንዳለባት ሲነግራት "ከሰው ሕይወት የሚበልጥ ነገር የለም" ብላ እንደሸኘችው ተናግሯል፡፡
 
ዶ/ር በየነ በሕክምናው ዓም ከ10 ዓመት በላይ ያገለገለ ሲሆን በእነርሱ ሙያ ማምሸትም ማደርም የተለመደ መሆኑን ያነሳል፡፡
 
በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top