ለቀጣይ አራት ዓመታት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት በእጩነት የቀረቡት ሰባት ግለሰቦች በዛሬው ዕለት "አትሌቲክሱ በማን ይመራ?" በሚል መሪ ሃሳብ ኢቲቪ ባዘጋጀው ውይይት ላይ ቀርበው ሀሳባቸውን አካፍለዋል።
ዕጩዎቹም ከሌሎች ተፎካካሪዎቻቸው የተሻለ ያስመርጠኛል ያሉትን ሀሳብም አቅርበዋል፡፡
ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በእጩነት የቀረቡት ኮማንደር ግርማ ዳባ የፌደሬሽኑን አጠቃላይ ችግር በዋናነት የአደረጃጀት፣ የስልጠና፣ ውድድርና የማዘውተሪያ ስፍራዎች እንደሆኑ ለይቻለሁ የመፍትሄ እቅድም አለኝ፤ ፌደሬሽኑ በገቢ እንዲጠናከር አደርጋለሁ ብለዋል።
ከጋምቤላ ክልል በእጩነት የቀረቡት ወ/ሮ ሪሳል ኦፒዮ፤ የተቋሙን አደረጃጀት የማሻሻል እቅድ እንዳለቸው አንስተው፤ አትሌቲክስ ሩጫ ብቻ ስላልሆነ እንደ ዝላይና ውርወራ ላሉ ስፖርቶች ትኩረት ሰጥቼ እሰራለሁ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ለአትሌቱ ፈተና የሆነውን የስፖርት ማዘውተሪያ እጥረት ላይ ማተኮር እና ተተኪ አትሌቶችን በማፍራት ላይም ሰፊ ስራዎች የመስራት እቅድ እንዳላቸው ገልፀዋል።
የኦሮሚያ ክልልን የወከለው አትሌት ስለሺ ስህን፤ የፌደሬሽኑን አደረጃጀት አዘምናለሁ ግልጸኝነት እንዲሰፍንም እሰራለሁ፤ በተጨማሪም ከሀብት ብክነት ጋር በተያያዘ ያለውን ክፍተትም ለማስተካከል ዝግጁ ነኝ ብለዋል፡፡
ፌደሬሽኑ ራሱን በሀብት እንዲያጠናክር እንደሚያደረጉና ሊገነባ ታቅዶ ያልተተገበረው የአትሌቲክስ መንደር ግንባታ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ተወካይ አቶ ያየህ አዲስ በበኩላቸው፤ "ረጅም የአመራርነት ልምዴ አትሌቲክሱን ለመለወጥ ይጠቅማል ብዬ አምናለሁ፤ ከባለሀብቶች ጋር እንደመስራቴ ለስፖርቱ የሚሆን ሀብት ለማሰባሰብ ያስችለኛል፡፡ ጥሩ ተግባቢ በመሆኔ ከሁሉም ጋር በቅርበት ለመስራት እችላለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ብመረጥ ተግባብዎት ችግር አይሆንም" ብለዋል።
ከትግራይ ክልል የቀረቡት አትሌት ገ/እግዚአብሄር ገ/ማርያም ደግሞ፤ ጥሩ የማስተባበር ችሎታ ስላለኝ ይህ ለአትሌቲክሱ መፍትሄ ለማምጣት ይጠቅመኛል፤ አትሌቲክሱ አንዱ የጎደለው ቅንነት በመሆኑ በመተሳሰብና በሰላማዊ መንገድ አስተባብሬ የመስራት አቅም አለኝ፡፡ ፌደሬሽኑ በፋይናንስ እንዲያድግም አደርጋለሁ ሲሉ ሀሳባቸውን አካፍለዋል።
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእጩነት የቀረቡተ አቶ ዱቤ ጅሎ፤ "ከ25 ዓመት በላይ አትሌቲክሱን ስለመራሁ ከ6ቱ ተወዳዳሪዎች የተሻልኩት እኔ ነኝ፡፡ ወርልድ አትሌቲክስና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ጋር ግንኙነት ስላለኝ ይህም ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት ይጠቅመኛል፡፡ አሁን ያለውን የአትሌቲክሱን ስብራት ለመጠገን በቂ ልምድ አለኝ" ብለዋል፡፡
ከድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የተወከሉት ኢንጂነር ጌቱ ግርማ በበኩላቸው፤ ትልቁ የአትሌቲክሱ ችግር የአመራር ስለሆነ ሰፊ አመራርነት ልምዴ የተሻለ ተመራጭ ያደርገኛል ብየ አምናለሁ ብለዋል፡፡
አሁን ላይ 2 የመሮጫ ትራኮች እያስገነባሁ ነው ብመረጥ ደግሞ የማዘውተሪያ ስፍራ ችግሮችን ለመፍታት ከዚህ በበለጠ እሰራለሁ፤ የአትሌቲክሱን ማህበረሰብ ወርጄ የማስተባበር አቅም አለኝ ሲሉም ተናግረዋል።
በአብርሃም አድማሱ