"የኢትዮጵያን አየር ኃይል ወደ ገናናነት ለማድረስ በቁጭት እየሰራን ነው" - የአየር ኃይሉ አባላት

1 Day Ago 110
"የኢትዮጵያን አየር ኃይል ወደ ገናናነት ለማድረስ በቁጭት እየሰራን ነው" - የአየር ኃይሉ አባላት

አየር ኃይልን ወደ ገናናነት ለማድረስ በቁጭት እየሰራን ነው ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ኃይል አባላት ገለጹ፡፡

ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ውጣ ውረዶች ያለፈው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከለውጡ ወዲህ ባለፉት አምስት ዓመታት የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች እያከናወነ እንደገኝ ይገለፃል፡፡

አየር ኃይሉ በቴክኖሎጂ እንዲዘምን እና ዓለም የደረሰባቸውን የጥገና ስራዎች ማከናወን እንዲችል ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑም ይጠቀሳል፡፡

በዚህ ሂደት አየር ኃይሉ በዋነኝነት የጥገና ማዕከሉን አቅም ማሳደግ ከግቦቹም መካከል ቀዳሚውን ደረጃ እንደሚይዝ የአየር ኃይሉ አባላት ይናገራሉ፡፡

በአየር ኃይል የኢንተርሴፕተር ጥገና ቡደን ኃላፊ የሆኑት ሻለቃ ዳዊት ተስፋዬ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በሪፎርሙ አማካኝነት ሰፋፊ ስራዎች ስለመጀመራቸው ገልጸዋል፡፡

በበረራ ወቅት እና ከበረራ በፊት የሚፈጠሩ ማንኛውንም ችግሮች ተቋሙ በራሱ አቅም የመፍታት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

ካለፉት 13 ዓመታት በላይ በብልሽት የቆሙ አውሮፕላኖችን በአየር ኃይሉ አባላት አማካኝነት በመጠገን ወደ አገልግሎት እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአቬሽን ጥገና ቁጥጥር ኃላፊ ሌተናል ኮለኔል ወንድምአገኝ ሻፊ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የጥገና ክፍል የአየር ኃይሉን የግዳጅ አቅም ማሳደግ የቻለ መሆኑን ገልፀው፤ "በቀን እና በለሊት ግዳጆችን እየፈጸምን እንገኛለን" ብለዋል፡፡

በአየር ኃይል ውስጥ ሀገሪቱን ወደተሻለ ከፍታ ለመውሰድ በቁጭት እየተሰራ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡

አንጋፋው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በቅርቡ የተመሰረተበትን 89 ዓመት ማክበሩ ይታወሳል፡፡

በሜሮን ንብረት  


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top