በሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስፈላጊው መሰረተ ልማት የተሟላላቸውና 5 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው የማምረቻ ሼዶች ለኢንቨስትመንት ዝግጁ ሆነው ባለሀብት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተገለጸ፡፡
የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአፋር ክልል ካለው መልካ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ለወጪ ንግድ ኢንቨስትመንት ተመራጭ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲ ገለጸዋል፡፡
የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአፋር ክልል ካለው ተፈጥሮ ሀብት እና መልካዓ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ምርት አቀነባብረው ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ ለሚያቀርቡ ኩባንያዎች ተመራጭ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከጂቡቲ ወደብ 280 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከአሰብ ወደብ በ290 ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ መገኘቱ ኤክስፖርት መር ለሆኑ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ፓርኩን እጅግ ተመራጭ እንደሚያደርገው አቶ ዘመን ጁነዲ ጠቁመዋል፡፡
የአፋር ክልል በግብርና ዘርፍ እና በተፈጥሮ ሀብት ረገድ ያለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ አካባቢው ሰላም የሰፈነበት መሆኑ እና ወጣት የሰው ሀይል ያለበት በመሆኑ ሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የገቡ ባለሃብቶችን መሳብ መቻሉን አቶ ዘመን አብራርተዋል፡፡
በፓርኩ ስራ ለመጀመር የሚያስችል የፋብሪካ ተከላ እና የሼድ ግንባታ እያከናውኑ ያሉ ባለሀብቶች አፋር ክልል የሚገኘውን ከፍተኛ የጨው ሀብት በፋብሪካ በማቀነባበር ለሰው እና ለእንሰሳት ምግብነት እንደሚያቀነባብሩ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡
ፋብሪካዎቹ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን የጨው ምርት እንደሚያመርቱም መግለጻቸውን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ከሚገኙ 177 ያህል የማምረቻ ሼዶች ውስጥ ከ 86 በመቶ በላይ የሚሆኑት በውጭና በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መያዛቸው ይታወቃል።