ዋሬን ቡፌት 99.5 በመቶ የሚሆነውን ሐብታቸውን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንደሚለግሱ ቃል ገቡ

17 Days Ago 226
ዋሬን ቡፌት 99.5 በመቶ የሚሆነውን ሐብታቸውን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንደሚለግሱ ቃል ገቡ
ባለሐብቱ የበርክሻየር ኩባንያ ሊቀመንበር ዋሬን ቡፌት 99.5 በመቶ ወይም ደግሞ 150 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሐብታቸውን ከሕልፈታቸው በኋላ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንደሚለግሱ ይፋ አድርገዋል።
 
የ94 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋው አሜሪካዊው ባለሐብት ሰኞ ዕለት ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የበርክሻየር የአክሲዮን ድርሻቸውን ለአራት በጎ አድራጎት ድርጅቶች መለገሳቸውም ተነግሯል።
 
ዋሬን ቡፌት ሰኞ እለት ለበርክሻየር ባለአክስዮኖቹ በጻፉት ደብዳቤ እንዳስታወቁት 99.5 በመቶ ሐብታቸውን በሦስቱ ልጆቻቸው አማካኝነት ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለመስጠት ተዘጋጅተዋል፡፡
 
"ከሕልፈተ ሞቴ በኋላ አጠቃላይ ያለኝን አሴት ልጆቼ ለበጎ አድርጎት ድርጅቶች እንደሚሰጡልኝ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል በጻፉት ደብዳቤ፡፡
 
እ.ኤ.አ በ2006 ጀምሮ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች አሴታቸውን በመለገስ የሚታወቁት ዋሬን ቡፌት አሁን ያደረጉትን ልገሳ ጨምሮ በድምሩ ከ58 ቢሊዮን ዶላር በላይ መለገሳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
 
ባለሐብቱ ከዚህ በፊት ከ43 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለቢልና ሚሊንዳ ጌት ፋዎንዴሽን መስጠታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ እስካሁን በበርክሻየር አክሲዮን ካላቸው ድርሻ ከ56 በመቶ በላይ ሐብታቸውን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለግሰዋል፡፡
 
ዋሬን ቡፌት ከሕልፈታቸው በኋላ ቀሪ የሐብት ድርሻውን በልጆቻቸው አማካኝነት በ10 ዓመታት ውስጥ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲሰጥ ወስነዋል።
 
የባለሐብቱን ውሳኔ ተከትሎ የበርክሻየር ድርጅት ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
 
በርክሻየር በዋሬን ቡፌት ሊቀመንበርነት የሚመራ በስሩ ከ1 ትሪሊዮን ዶላር የሚልቅ ሐብት የሚያንቀሳቅስ ኩባንያ ነው፡፡
 
በመሐመድ ፊጣሞ
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top