ከግማሽ ቢሊዮን የሚልቅ ህዝብን የምግብ ዋስትና አረጋግጦ እንዴት ከረሃብ ነጻ ዓለምን መፍጠር ይቻላል?

4 Days Ago 268
ከግማሽ ቢሊዮን የሚልቅ ህዝብን የምግብ ዋስትና አረጋግጦ እንዴት ከረሃብ ነጻ ዓለምን መፍጠር ይቻላል?

እስከ 864 ሚልዮን የሚደርሱ ሰዎች እንዴ ከተመገቡ የሚቀጥለውን ምግባቸውን ከየት እንደሚያገኙ እርግጠኞች አይደሉም። ዛሬ በዓለም ላይ 733 ሚሊዮን ሕዝብ ወይም ከ11 ሰዎች አንድ ሰው በከፍተኛ ረሃብ ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ አፍሪካ ከፍተኛውን ድርሻ የምትይዝ ሲሆን፣ 20 በመቶ ሕዝቧ በከፍተኛ ረሃብ ውስጥ ይገኛል፡፡ ላቲን አሜሪካ እና እስያ በተከታታይ 8 እና 6 በመቶውን ይይዛሉ፡፡ ዓለምን ከረሃብ ነጻ ማድረግ ይቻላል በተባለበት 2030 ዋዜማ 582 ሚሊዮን ሕዝብ የረሃብ አደጋ የተጋረጠበት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ከአፍሪካ እንደሆነ የተመድ ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡ 

ኢንዱስትሪን በማስፋፋት፣ ቴክኖሎጂ በመጠቀም እና አግሪ ቢዚነስን በማስፋፋት ረሃብን ከዓለም ማጥፋት ይቻላል በማለት ነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት(UNIDO) ከረሃብ ነጻ ዓለምን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ያለው፡፡ ድርጅቱ ሁሉም ሰው አካላዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታውን የሚያሻሽል፣ በቂ፣ አስተማማኝ እና ገንቢ ምግብ ማግኘት አለበት በሚል እየሠራም ይገኛል። ምርቶች ላይ እሴትን በመጨመር ገቢን በማሳደግ ይቻላል የሚለው ድርጅቱ፣ ለዚህ ደግሞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል ይላል፡፡

በአውሮፓውያኑ 2030 ረሃብን ከዓለም ለማጥፋት የተያዘው ዕቅድ በኮቪድ 19፣ በግጭቶች፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በሌሎች የተለያዩ ተግዳሮቶች ምክንያት ፈተና እንደገጠመው የሚገልጹት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ገርድ ሙለር፣ አሁንም ዓለም ከተባበረ ከረሃብ ነጻ ዓለምን መፍጠር ይቻላል ይላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ወሳኝ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

 

ድርጅቱ እየሠራቸው ካሉት ሥራዎች መካከል የድህረ ምርት ብክነትን መቀነስ ነው፡፡ ይህ የሚሳካው ደግሞ የግብርና ምርቶች ማቀነባባሪያ መንገዶችን በማመቻቸት እንደሆነም የድርጅቱ አቋም ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎቹን ማስፋፋት የምግብ ብክነትን ከመቀነሱም በላይ በገጠር ለሚገኙ ሰዎች የሥራ ዕድልን በመፍጠር እና ገቢያቸውን በማሳደግ የምግብ ዋስትነናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል፡፡

በታዳጊ ሀገራት ምርታማነትን ማሳደግ እና የግብርና ውጤቶችን ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድልን ከማስፋፋት በተጨማሪም የተቀነባበሩ የግብርና ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ የሀገርን ኢኮኖሚ ያሻሽላል፡፡ ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችም የራሳቸው ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ የግብርና ምርቶችን መረጃ የሚሰጡ መተግበሪያዎች እና ዲጂታል አገልግሎቶች የግብርና ምርቶችን አቅርቦት እና ሰንሰለቶችን መረጃ ሥርዓት ያሻሽላሉ፡፡

የዲጂታል ቴክኖሎጂ የዕውቀት ሽግግር ሴቶችን እና ወጣቶች በግብርና ምርቶች አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ብክንትን እንዲቀንሱ፣ ጥራትን እንዲጠብቁ እና የምግብ ተደራሽነት እንዲያሻሽሉ ይረዳቸዋል፡፡ የምግብ ደህንነት እና የምግብ ጥራት ቁጥጥር የሰዎችን ጤንነት ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን አኗኗርንም ለማሻሻልም ቁልፍ ናቸው።

የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ የተቀነባበሩ የግብርና ምርቶች የሚላኩበት ገበያ ማግኘት በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ገበያውን ለማግኘት ደግሞ አስተማማኝ የአቅርቦት ሰንሰለትን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጀመረችው ጉዞ

ባለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘመናዊነት በማጎልበት የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል የግብርና ሪፎርም እየተገበረች ትገኛለች፡፡ የግብርና ሪፎርሙ የአርሶ አደሩን አቅም በማጎልበት በዘርፉ ላይ ያሉ መዋቅራዊ ችግሮችን በመቅረፍ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ያተኮረ ነው። የገጠሩን ማኅበረሰብ አኗኗር ለማሻሻል የሚያስችሉ እና የግብርና ምርቶች ገበያ የሚያገኙበት ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘውን ግብርናን ማዘመን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ነው፡፡

መንግሥት ምርታማነትን ለማሳደግ እና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱን ለመደገፍ ከእለት ፍጆታ ምርቶች ባሻገር ገቢ የሚያስገኙ ምርቶችን እንዲመረቱ እያበረታታ ነው። የሰብል አመራረት ስብጥርን በማሳደግ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን እንደ ቡናና ቅመማ ቅመም እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ላይ ያተኮሩ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።

ኢትዮጵያ በስትራቴጂ በመምራት ውጤታማ ከሆነችባቸው የግብርና ምርቶች መካከል የመስኖ ስንዴ ልማት በስንዴ ምርት ራሷን እንድትችል አድርጓታል። ይህ ፕሮግራም በተለይ ቆላማ አካባቢዎች ስንዴ አምራች እንዲሆኑ ያስቻለ እና ጠፍ የሆነው ሰፊ መሬት ምርታማ እንዲሆን ያደረገ ነው፡፡ በዚህም ስንዴ አምርተው የማያውቁ እንደ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቦረና እና ሀረርጌ አካባቢዎች ሰፊ የስንዴ ማሳ እንዲታይባቸው አድርጓል።

በዚህ ውጤታማ የስንዴ ምርት እና በአረንጓዴ አሻራ ባመጣችው ተጨባጭ ለውጥም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) አግሪኮላ ተሸላሚ ሆናለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሰጡት አመራር ይህን የተከበረ ሽለማት በሮም ተሸልመዋል።

በግብርና ለሚሰማሩት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ባለሀብቶች የእርሻ መሬትን በአነስተኛ ኪራይ ወስደው እንዲያለሙ ዕድሎች ተመቻችተዋል። መንግሥት በግብርና ግብአቶች እና ቴክኖሎጂዎች ላይ የነበረውን ቀረጥ በማንሳት ዘርፉን እየበረታታም ይገኛል፡፡ ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ የሚደረገው ከፍተኛ ዓመታዊ ድጎማ የአርሶ አደሩ ምርታማነት እንዲጨምር አስችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ "ከረሃብ ነጻ" ከሚለው ዓለም አቀፋዊ ንቅናቄ ጋር በመስራት ላይ ትገኛለች። እየተገበረችው ያለው ሪፎርም ግብርናን ማዘመን፣ ምርታማነትን በማሻሻል እና የአርሶ አደሮችን የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም በማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው።

አርሶ አደሩ ጥራት ያለው ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ እና የመስኖ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን መንግሥት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ተባዮችን እና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች በተለይም እንደ ጤፍ፣ ስንዴ እና በቆሎ ያሉ ሰብሎች ምርታማነትን ለማሳደግ የተሠራው ሥራ ውጤታማ ሆኗል።  

አርሶ አደሩ የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ምርታማ እንዲሆን እየተሠራ ሲሆን፣ የዝናብ ውኃን ሰብስቦ መጠቀም እና አነስተኛ መጠን ያለው መስኖን በማስፋፋት ዓመቱን ሙሉ ማምረት የሚቻልበት ዕድል እንዳለ ተረጋግጧል።

በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ የደን ሽፋንን በማሳደግ ድርቅ የሚያስከትለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ኢትዮጵያ በዚህ እንቅስቃሴ የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ የግብርና ምርታማነት ሊያሻሽሉ የሚችሉ 40 ቢሊዮን ችግኞችን ተክላለች፡፡ እነዚህ ችግኞች የደህንነት ጠቀሜታ ብቻ ያላቸው ሳይሆን የምግብ ዋስትናንም የሚያሻሽሉ ስለመሆናቸው እየደረሱ ያሉት ፍራፍሬዎች ማሳያ ናቸው፡፡

መንግሥት ግብርናውን ውጤታማ በማድረግ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ፍሬያማ ለማድረግ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት ለመጨመር የሚያስችሉ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎችን አስፋፍቷል። ይህ "ኢትዮጵያ ታምርት" እንቅስቃሴ ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን የፈጠረ ሲሆን፣ በተለይም ቡና እና የቅባት እህሎችን በማቀነባበር ወደ ውጭ ለመላክ የሚያችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።

ግብርናን ዲጂታል በማድረግ ውጤታማነቱን ለማሻሻል አጽንኦት ተሰጥቷል። አርሶ አደሮች እና ሌሎች በዘርፉ ላይ የተሰማሩ አካላት ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በመጠቀም የገበያ ሁኔታን እና ቦታዎችን፣ የአየር ሁኔታን እና ሌሎች ከምርታማነት ጋር መረጃ በማግኘት ውሳኔ ለማድረግ እየተጠቀሙበት ነው።

ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ ረሃብን ከዓለም ለማጥፋት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ የሚሳካው ግን በትብብር ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ገርድ ሙለር ኢትዮጵያ ባስተናገደችው “ከረሃብ ነጻ ዓለም ኮንፈረንስ” ላይ እንደተናገሩት ዓላማውን ለማሳካት ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት በየዓመቱ ተጨማሪ 50 ቢሊዮን በድምሩ 500 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ከረሃብ ነጻ ዓለምን ለማሳካት በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት ቃላቸውን እንዲጠብቁ ነው ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ ያቀረቡት፡፡ ሀገራት ለመከላከያቸው ከሚመድቡት 2 በመቶውን ብቻ ለዚህ ተግባር ለማዋል ቁርጠኛ ቢሆኑ ዓላማውን ለማሳካት እንደሚቻልም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡ ኢትዮጵያ ችግሩን ለመጋፈጥ የወሰደችውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና ያመጣችውን ለውጥም አድንቀዋል፡፡

በለሚ ታደሰ 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top