"የግል ህልም የወል ህልምን ማጨናገፍ የለበትም" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

1 Mon Ago 548
"የግል ህልም የወል ህልምን ማጨናገፍ የለበትም" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

"በትናንት ውስጥ ወረት እና እዳ በዛሬ ውስጥ እድል እና ፈተና በነገ ውስጥ ተስፋ እና ስጋት ስላለ ኢትዮጵያዊያን የጋራ እጣ ፈንታችንን በጋራ መወሰን አለብን" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለከፍተኛ አመራር አካላት በሰጡት ሥልጠና፡፡

የሚጋሩት የጋራ ህልም ያላቸው ህዝቦች ነጋቸውን በማይናድ ጠንካራ መሰረት ላይ ያኖራሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአንድነት የሚያቆማቸው አካላዊ፣ ምናባዊ እና ሥርዓታዊ ውቅር አላቸው ብለዋል፡፡ 

ማንም ከመሬት ተነስቶ እንዳይዳፈረን ህልም ያነገብን፣ ህልምን የሰነቅን፣ ህልምን የምንናገር፣ የሚተገበር ተሻጋሪ ህልም ያለን ህዝቦች መሆን አለብን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የጋራ ህልም ጊዜን ተሻጋሪ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ህልም ልዕልና መር ሲሆን ጊዜን ተሻጋሪ ለትውልድ የሚተርፍ ይሆናል ብለዋል፡፡

መነሻው በቀል እና የበላይነትን ማረጋገጥ የሆነ ሀሳብ ቅዠት እንጂ ህልም አይሆንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ እንደዚህ ዓይነቱ ስሁት ስሌት በጥላቻ ላይ ያተኮረ ባዶ ምኞት ስለሆነ መጨረሻው ጥፋት ነው ሲሉም አክለዋል፡፡  

ህልም ግልጽና ቀጥተኛ፣ አሳታፊና አካታች፣ ቀጣይና አዳጊ እንዲሁም ተተግባሪ መሆን እንዳለትም ገልጸዋል፡፡

የወል ህልም፣ አዎንታዊ እና መልካም ገጽታ፣ የጋራ አቅጣጫ እና ዓለማ፣ ህብረት እና አንድነት፣ ፈጠራ እና ትጋት ሲኖረው በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ይንጸባረቃልም ነው ያሉት፡፡

የህዝቦች ትብብር፣ የዜጎች ክብር፣ ሰብዓዊ ብልጸግና፣ ሀገራዊ ልዕልና የኢትዮጵያ ህልም መሰረታዊያን መናቸውን ጠቅሰው፤ ይህ እንዲሳካ ዜጎች በሰፈር እና በብሔር መከፋፈል የለባቸውም ብለዋል፡፡

በሕዝብ አገልጋይነት ህልማችንን ለማሳካት ለሀገር እድገት በመሥራት የብልጽግና ፊታውራሪ መሆን እንችላለን ሲሉም ነው ያወሱት፡፡

ወጣት ሀገር እና ህዝብ አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጋራ ትርክት እና ራዕይ በመጋራት ከደም ባሻገር በላብ እና በሀሳብ የሚተሳሰር ወጣት መፍጠር መቻል አለብን ብለዋል፡፡

ትውልዱ ለመጪው ዘመን የተዘጋጀ፣ መጪውን ዘመን አሁን ላይ ምቹ አድርጎ የሠራ፣ ከቴክኖሎጂ የተዛመደ እና ከአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር አብሮ መጓዝ የሚችል ለማድረግ የወል ህልም እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡

ወጣቶች የዲጂታሉ ዓለም ፈር ቀዳጆች የሰላም እና የእርቅ አምባሳደሮች መሆን እንደሚገባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

ሁሉም ሰው የግል ህልም እንዳለው ጠቅሰው፣ የግል ህልም የጋራ ህልምን የሚገዳደር መሆን የለበትም ብለዋል፡፡

የግል ህልም የጋራ ህልምን የሚያጨናግፍ ሳይሆን ለጋራ ህልም ስኬት ግብአት መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

በመሃመድ ፊጣሞ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top