“የበረሃው ገነት”

1 Day Ago 89
“የበረሃው ገነት”
ለመጀመርያ ጊዜ ላየው ሰው ከሀገር ውጭ ያሉ ቅንጡ የመዝናኛ ስፍራዎችን ሊመስለውና እንዲገምትም ሊያደርገው የሚችለውን አስደማሚ ውበት የተላበሰ የምድር ገነት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
 
ይህ ውብ መንደር ቤኑና ነው።
 
እንዴት በዚህ ልክ ብሎ ለሚጠይቅ አካባቢው ወደ ውብ መንደርነት ከመሸጋገሩ በፊት እልም ያለ የሚባልለት በረሃ፣ በአሲዳማነት የተጠቃ መሬት፣ ውኃው ያልታከመ፣ ለኑሮ ምቹ ያልሆነ ይህማ ምንም አይበቅልበትም ሰውም አይኖርበትም የተባለ ስፈራ መሆኑ ነው።
 
ለዛ ነው ሀገር ሳይሰማ ሀገር ወዳድ ግለሰቦች በረሃማ የሆነውን ክፍል ወደ ምድር ገነትነት ቀይረው ለነገ የሀገር ተስፋ ማሳያ የለፉት።
 
ለፍተው አልቀሩም ውኃውንም መሬቱንም አክመው ለኑሮ ምቹ እንዲሆን አሰናድተው የበሰቃውን ቤኑና መንደር ገንብተው እንካችሁ ያሉን።
 
በሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ሥድስት ዓመታት ብዙ የልማት ስራዎች ተሰርተዋል።
 
በተለይ ግን የተፈጥሮ ሐብቶቻችንን ተጠቅሞ እና እሴት ጨምሮ የቱሪዝም ሴክተሩን ከፍ ማድረግ ላይ አስደናቂ የሚባሉ ፕሮጀክቶች ከመነደፍ አልፈው መሬት ላይ ወርደው ለህዝብ ክፍት ከተደረጉ ቆዩ።
 
ከነዚህም መሀል የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት፣ ወንጪ ኢኮ ሎጅ፣ ሀላላ ኬላ ሪዞርት እንዲሁም የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅን ጨምሮ በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ የተሰሩትን መጥቀስ ይችላል።
 
እነዚህን ፕሮጀክቶች መንግስት ቢሰራቸውም የማስተዳደር ኃላፊነቱ ደግሞ በዘርፉ ሰፊ ዓለም አቀፍ ልምድ ላለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አካል ለሆነው ለስካይላይት ሆቴል ተሰጥተዋል።
 
አሁን ደግሞ አስደናቂ እንደሆነ የተነገረለትና ከአዲስ አበባ በአዳማ የፍጥነት መንገድ በመጓዝ በጥቂት መቶ ኪሎ ሜትሮች እርቀት በመተሀራ እምብርት ላይ ያረፈ ትክክለኛ የኢትዮጵያ ማሳያ ጌጥ የበረሃው ገነት ቤኑና መንደርን እናገኛለን።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለ ቤኑና መንድር “መንደሩ ይቻላል የሚለውን ቃል በዓይናችን ያየንበት፤ በእጃችን የጨበጥንበት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
 
ይህም ሲገለጥ ይቻላል መፈክር ሳይሆን በስራ የተፈተነ በውጤት የታጀበ የሚጨበጥ የሚነካ የሚታይ ስለመሆኑ ቤኑና መንደር ማሳያ ነው።
 
ይህ አስደናቂ መልክአምድር በባሕላዊና ዘመናዊ ዘውግ የተቃኘ ኪነ-ህንፃን የተላበሰ የተለፋበትና የተደከመበት ስለመሆኑ ወደቦታው ሄደው ምስክርነት የሰጡ ሰዎች ይቅርና በቴሌቭዥን መስኮት የተመለከቱት ይናገራሉ።
 
ቤኑና መንደር በግል ሴክተሩ እውቀትና ገንዘብ እንዲሁም ጉልበት ብሎም በዩናይትድ ዓረብ ኢምሬትስ መንግስት ትብብር የተሰራ ነው።
 
ያ ለማልማት አይደፈርም የተባለው በረሃማው የበሰቃ አከባቢ ዛሬ ላይ ቤኑና ሆኖ ፍራፍሬ የሚመረትበት፣ በስጋና ወተት ከብቶች የተሞላ፣ ከ500 በላይ ዕንቁላል በቀን በሚጥሉ ዶሮዎች ግብዓትን የሚያስገኝ ለብዙዎች የስራ እድል ፈጥሮ ወጥተው እንዲገቡ በአካባቢያቸው እንዲጠቀሙ በሌማት ቱርፋቱ የልማቱ ተቋዳሽ እንዲሆኑ ያደረገ ስፍራ ሆኖ ስሙ ተቀይሯል።
 
ይህ ስፍራ የተሰራው ለህዝብ ነው ። ወደ ቦታው ለሄደ ሰው በ30 ኪሎ ሜትሮች እርቀት አዋሽ ብሔራዊ ፓርክን ሊጎበኝ ይችላል ። በዛው 30 ኪሎ ሜትር እርቀት የገበታ ለሀገሩ የአፋር ክልል “ፓልም” ስለሚገኝ በአንድ ድንጋይ ሦስት ቦታ የሚባለውን ተረት በተግባር ገለጠ ማለት ነው።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “አሁን ላይ በሀገሪቱ ብዙ አካባቢዎች ያለንን ተፈጥሮ ለገበያ የምናቀርብባቸው ኢትዮጵያን የሚመጥኑ ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል። አርባ ምንጭ፣ ጅማ፣ ሸበሌ፣ ገረአልታ፣ ሐይቅና ደንቢ ጀምረናቸዋል እንጨርሳቸዋለን” ብለዋል።
 
ቤኑና መንደር ግን አዲስ ውበት፤አዲስ ጥበብ፤አዲስ አሸናፊነትን ለኢትዮጵያን እየገለጠ በበረሃማው በሰቃ መተሀራ አቅራቢያ “የበረሃው ገነት” ሆኖ ኢትዮጵውያንን ይጠብቃል።
 
በናርዶስ አዳነ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top