ለኤሎን መስክ በዶናልድ ትራምፕ የተሰጠው አዲሱ ስራ ምንድን ነው?

1 Day Ago 53
ለኤሎን መስክ በዶናልድ ትራምፕ የተሰጠው አዲሱ ስራ ምንድን ነው?
ባለሐብቱ የኤክስ እና የተስላ ኩባንያ ባለቤት ኤሎን መስክ፣ በቅርቡ በተመረጡት 47ተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ የመጨረሻ ወራት ወቅት ጠንካራ ደጋፊ ሆነው ብቅ ማለታቸው ይታወሳል።
 
ይህንን ድጋፍ ያልረሱት ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለቢሊየነሩ ኤሎን መስክ ሹመት መስጠታቸው ተሰምቷል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢሊየነሩን ኤሎን መስክ አዲስ ባቋቋሙት የመንግስት መስሪያ ቤቶች አፈጻጸም ዲፓርትመንት (ዲኦጂኢ) መሪ አድርገው ነው የሾሟቸው።
 
ከመንግስት መዋቅር ውጪ እንደሆነ የተገለፀውና አዲስ የተመሰረተው ተቋም ተግባሩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን አፈጻጸም መፈተሽና መዋቅራዊ ማስተካከያ ለማድረግ ሀሳቦችን ማቅረብ መሆኑም ተነግሯል።
 
አዲሱ ተቋም አሜሪካ ለዓመታዊ ወጭዋ ከመደበችው 6.5 ትሪሊዮን ዶላር ላይ የሚባክነውንና በሙስና የሚጭበረበረውን ሐብት እንደሚያተርፍም ታምኖበታል።
 
አዲሱን ተቋም ከኤሎን መስክ ጋር በመሆን የባዮ ቴክኖሎጂ ስራ ፈጠራ ባለሙያው ቪቪክ ራማስዋሚ በጋራ እንደሚመሩት ቢቢሲ ነው የዘገበው።
 
ሹመቱን አስመልክቶ ዶናልድ ትራምፕ በሰጡት ሀሳብ" የተሾሙት ሁለቱ ሰዎች በእኔ አስተዳደር ዘመን የመንግስት ቢሮክራሲን፣የበዛ ቁጥጥርን እና ለብክነት የሚያጋልጡ ወጭዎችን ለመቀነስ መንገድ ይከፍታሉ" ብለዋል።

አዲሱን ተቋም የዘመናችን "የማንሃታን ፕሮጀክት" በማለት አሜሪካ አቶሚክ ቦንብ ለመስራት ከተጠቀመችበት የፕሮጀክት ስም ጋር አነፃፅረው አንስተውታል።

 
ከሹመቱ በፊት ኤሎን መስክ በ"ኤክስ"(ትዊተር) ገፁ ላይ በለጠፈው ፅሁፍ "በመንግስት የስራ ሂደት ውስጥ ብዙ መወገድ ያለባቸው አላስፈላጊ አሰራሮች አሉ "ማለቱ አይዘነጋም።
 
ሹመቱን ያገኘው ቢሊየነሩ ኤሎን መስክ ትራምፕ በድጋሚ ለመመረጥ ባደረጉት ፉክክር በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በማውጣት ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።
 
በናርዶስ አዳነ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top