13ኛው የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

24 Days Ago 239
13ኛው የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ላኪዎች ማህበር ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 13ኛ የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መካሄድ ጀምሯል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ጉባኤውን በንግግር ያስጀመሩ ሲሆን የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች የውጪ ምንዛሪ በማስገኘት ለሀገራችን ኢኮኖሚ፣ ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች እና ለብሄራዊ የኢኮኖሚ እድገት የጀርባ አጥንት የሆኑ የግብርና ምርቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ ሀገራችን ካሏት እምቅ ሀብቶች በተለይም ሰሊጥና ሌሎች የቅባት እህሎችን ጨምሮ የጥራጥሬ ምርቶች የዓለም አቀፍ ገበያ ፍላጎት የሚፈልገውን መስፈርት ባሟላ መልኩ በጥራት እና በብዛት እያመረተች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲን በቁርጠኝነት እየተገበረች ሲሆን መንግስት የአለም የንግድ ድርጅት አባልነት ድርድርን ከሁለት ዓመታት በኋላ ለማጠናቀቅ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተጨማሪ የቅባት እህሎችና የጥራጥሬ ምርቶችን እሴት ጨማሮ ለመላክ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ይህም የወጪ ንግድ ግኝትን ለማሳደግ፣ ለስራ እድል ፈጠራ እና ለአጠቃላይ ሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጾ እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡

ዛሬ የተጀመረው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በኤግዚቢሸን፣ በውይይት እና በልዩ ልዩ መርኃ ግብሮች እስከ ህዳር 11 ቀን 2017 ድረስ እንደሚቆይ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top