በአዲስ አበባ ከተማ ለእሳትና ድንገተኛ አደጋ መንስኤ የሆኑ 5 ዋና ዋና ምክንያቶች

1 Hr Ago 338
በአዲስ አበባ ከተማ ለእሳትና ድንገተኛ አደጋ መንስኤ የሆኑ 5 ዋና ዋና ምክንያቶች

በአዲስ አበባ ከተማ በኃይልና በንብረት አጠቃቀምና አያያዝ እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች እየደረሱ ያሉ ጎርፍን ጨምሮ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች በሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ።

በ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ የደረሱ 127 የእሳት፣ የጎርፍና ሌሎች አደጋዎች ለ22 ሰዎች ሞት፣ ለ12 ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ምክንያት መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሸነር አቶ ጥላሁን ቶላ በተለይ ለኢበሲ ሳይበር ገልፀዋል።

አደጋዎቹ 94 ሚሊዮን ብር በሚገመት ሀብት ላይ ውድመት ማስከተላቸውንና 2.46 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ግን ማዳን መቻሉን ነው ምክትል ኮሚሽነሩ ያስታወቁት።

በ2016 ዓ.ም ከደረሱ 523 ድንገተኛ አደጋዎች ኮሚሽኑ በወሰዳቸው ፈጣን እርምጃዎች 37 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ማዳን ቢቻልም፤ 1.26 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ወድሟል።

በአንድ ተቋም ወይም ግለሰብ ሳቢያ በሚከሰቱ አደጋዎች ለአብነትም በአቃቂ፣ በሾላ እና በመርካቶ አከባቢዎች በድንገተኛ አደጋዎች ምክንያት ከፍተኛ ውድመት ደርሷል ብለዋል።

በህንፃዎች አያያዝና አጠቃቀም ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ጠቅሰው፤ በደንብ ማሰብ አለብን፣ ምንም ዓይነት መዘናጋት አያስፈልገም፣ ቅፅበታዊ ክፍተት ከፍተኛ ውድመት ያስትላል ሲሉ አሳስበዋል።

በከተማዋ ለሚከሰቱ ድንገተኛ የእሳት አደጋዎች ዋናዎቹ መንስኤዎች 5 መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ጥላሁን ቶላ፤ ከነዚህ አንደኛው የኃይል አጠቃቀምና አያያዝ ክፍተት መሆኑን አንስተዋል።

ትክክለኛውን የኤሌክትሪክ መጠን አለመጠቀም፤ የኤሌክትሪክ ዝርጋታን በባለሙያ ያለመዘርጋት፤ የላላ የኤሌክትሪክ መስመር መነካካት፤ የሶኬትና የማከፋፋያ አጠቃቀም ውስንነት፤ ገቢ ኃይል እና የሚጠቀሙት ኃይል አለመመጣጠን እንዲሁም የአሌክትሪክ ዕቃዎች የጥራት ችግር ተጠቃሽ መንስኤዎች ናቸው ብለዋል።

ሁለተኛው የንብረት አያያዝና አጠቃቀም ክፍተት ሲሆን፤ ይህም በቤት ወይንም በህንጻ ውስጥ ግብዓትን፣ ማምረቻን፣ ምርትን እና መሸጫን በአንድ ቦታ ማድረግ፤ የተለያየ ባህሪ ያላቸው ዕቃዎችን በአንድ ቦታ ማድረግ፤ ህንፃው ከተገነባበት ዓላማ ውጪ ለተለያዩ ድብልቅ ጉዳዮች መጠቀምን እና የመሳሰሉትን ያካትታል።

ተቋማት ህንጻቸውን የአደጋ ደህንነት የማስፈተሸ ተገቢውን የአደጋ ደህንነት መስፈርቶችን እንዲሟሉ ያለማድረግ፤ የሚሰጣቸውን ግንዛቤ ተግባራዊ ያለማድረግ፤ ትላልቅ ህንጻዎች የአደጋ ደህንንት ባለሙያ ያለመቅጠር ስጋቶችን ያለማረም ክፍተቶች ይታያል ነው ያሉት።

የተቋማት የአደጋ ደህንነት ሁኔታ ማለትም ተቋማት የአደጋ ደህንነት ብቃት ደረጃ ለማረጋገጥ ጥረትም ፍላጎት አለመኖር ሶስተኛው መንስኤ ሲሆን ይህም ከግንባታ በፊትና በግንባታ ወቅት የአደጋ ደህንነት ብቃት የሚያረጋግጡ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት አለመኖር ነው ብለዋል።

ነዋሪው የአደጋ ደህንነትን ባህል በማድረግ፤ አደጋን በራስ አቅም የመቋቋም ፍልጎትና አቅም በመፍጠር ረገድ ሰፊ ክፍተት መታየቱና የህብረተሰብ የአደጋ ደህንነት ባህል አለመኖርና መዘናጋት 4ኛው የአደጋ መንስኤ መሆኑን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል።

በከተማዋ የሚገነቡ ቤቶችና ህንጻዎች በአብዛኛው የሚገነቡበትን አከባቢ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የዲዛይን ስታንዳርድ፣ ዲዛይንና ግንባታ በሚፈለገው ደረጃ ያለማድረግ፤ ግንባታዎቹ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን መቋቋም እንዲችሉ የአደጋ ደህንነትን አሟላተው በሚፈለገው መጠንና ጥራት አለመገንባት፤ ከግንባታ በፊት፣ በግንባታ ወቅትና በመጠቀም ሂደት የአደጋ ደህንነታቸውን በሚመለከተው ተቋማ አለማረጋገጥ 5ኛው መንስኤ መሆኑን ያነሳሉ።

በየጊዜው የሚከሰተውን የእሳትና ድንገኛ አደጋ መጠን ለመቀነስ ህብረተሰቡ የአደጋ ግንዛቤ ማሳደግ፣ የተቋማትን የአደጋ ደህንነት ደረጃ ማረጋገጥና በባለሙያ መታገዝ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ተቋማት ማሟላት ያለባቸውን የአደጋ ደህንነት ማሟላት፤ ከግንባታ በፊት፣ በግንባታ ወቅትና በመጠቀም ሂደት የአደጋ ደህንነትን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎችን በመስራት ደህንነታቸውን በየጊዜው ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑንም ገልፀዋል።

ህንጻዎች ለተገነቡበት ዓላማ ብቻ ማዋል፤ የአደጋ ደህንነት ስታንዳርዶችን የሚያሟሉ ግብዓቶችን መጠቀም፤ እሳትንና ጎርፍ የሚቋቋሙ ግብዓቶችን መጠቀም፤ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ መስመጥንና መሬት መናድን ታሳቢ ያደረጉ ግንባታዎችን መገንባት፣ አደጋውን ለመቀነስ ጠቃሚ እርምጃዎች ናቸው ብለዋል።

"እየወደመ ያለው የሀገር ህብት ነው፤ የሁሉም ማህበረሰብ ጉዳት ነው፤ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ የሻል" ያሉት አቶ ጥላሁን፤ ለአደጋ ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት ከግንባታ በፊት በግንባታ ወቅትና በአጠቃቀም ጊዜ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ አደጋ መቀነስ እንደሚቻልም ተናግረዋል።

በላሉ ኢታላ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top