ከራሱ በላይ ሀገሩን የሚያስቀድም ሠራዊት

3 Hrs Ago 84
ከራሱ በላይ ሀገሩን የሚያስቀድም ሠራዊት

ለደቂቃ እንኳ እረፍት ሳያምራቸው፣ የግል የሚባል ሕይወት አጣጥመው ሳይኖሩ ለኢትዮጵያ ክብር ይዋደቃሉ። ከጀግኖች አያቶቻቸው እና አባቶቻቸው የተረከቧትን ኢትዮጵያን ከነ ክብሯ እና ነጻነቷ በተሻለ ልዕልና ለልጆቻቸው ማስተላለፍ ነው ዓለማቸው። ሁሌም ደስታቸውን እና ስኬታቸውን የሚለኩት በኢትዮጵያ ክብር እና ልዕልና ነው። በተሰማሩባቸው ግዳጆች ሁሉ በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ጠብታ ውሃ ተካፍለው ግዳጃቸውን በአኩሪ ድል ይወጣሉ። "ከራስ በላይ ለሀገር" የሚለው ፅኑ ቃላቸው ሁሌም እንደተጠበቀ ነው። በሰላምም ሆነ በጦርነት ጊዜ ለሕዝባቸው መከታ እና መኩሪያ ናቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች።  

"የኩሩ ሕዝቦች መኖሪያ------- የህብረብሔር ቡቃያ፣

የሰላም ተምሳሌት ዓርማ ----የቀለሞች ህብር ኢትዮጵያ፤

በደም አሻራሽ አትመው -----ህዝቦች ለሰጡን አደራ፣

ለህገመንግሥቱ ክብር -------ታጥቀን ቆመናል በጋራ።" ይላሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መዝሙር የመጀመሪያዎቹ ስንኞች።

  1. ታሪካዊ ዳራ

ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምረው ውትድርና ባህላቸው ነው። በሰላም ጊዜ ትጉህ ሠራተኛ በጦርነት ጊዜ ምርጥ ወታደር መሆን ኢትዮጵያውያን የኖሩበት ባህል ነው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ኢትዮጵያ የማንንም ድንበር ተጋፍታ፣ ማንንም ወርራ ባታውቅም በተደጋጋሚ ግን ትንኮሳ እና ወረራ አጋጥሟት ያውቃል።

ኢትዮጵያውያን ከውጭ የሚቃጡ ትንኮሳዎች እና ወረራዎችን አርሶ አደሩ ሞፈርና ቀንበሩን አስቀምጦ ጦርና ጋሻ በመያዝ፣ የጀግና እናትም ልጇን መርቃ በመሸኘት፣ የቀረው ሕዝብ ደግሞ ደጀን በመሆን በአንድነት መክተዋቸዋል።

በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ሠራዊት ወደ መደበኛ አደረጃጀት እንዲመጣ እና ወታደር ደመወዙ ከሕዝብ ሳይሆን ከመንግሥት እንዲቆረጥለት ሙከራ ተደርጓል። አጼ ምኒሊክም የሠራዊቱን አደረጃጀት ሳያስተካክሉት የዓድዋ ጦርነት ተከሰተ። ኢትዮጵያውያንም በተለመደው ጀግንነታቸው ጣሊያንን በዓድዋ ተራሮች ድል ነስተው የጥቁር ሕዝቦችን እና የዓለም ጭቁን ሕዝቦችን የድል ሻማ ለኮሱ። 

ጣሊያን በተደራጀ ሠራዊት ያደረገችው ወረራ ያስተማራቸው የሚመስለው አጼ ምኒሊክ ዘመናዊ የሠራዊት አደረጃጀት እንደሚያስፈልግ ተገነዘቡ። በአጼ ቴዎድሮስ የተጀመረው የመደበኛ ሠራዊት አደረጃጀት ሙከራም ተሳክቶ የመከላከያ ሚኒስቴር የተቋቋመው ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም ነበር። የመጀመሪያው መከላያከያ ሚኒስትር ደግሞ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (ሀበቴ አባ መላ) ናቸው።

በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትም ዘመናዊ የሠራዊቱ አደረጃጀት ቀጥሎ የማዕረግ አሰጣጡም ዓለም አቀፍ ሆነ። በአምስቱ ዓመት ወረራ ጣሊያን ጊዜያዊ ድል ያገኘው ባልተመጣጠነ አቅም ምክንያት መሆኑን የተረዱት አጼ ኃይለ ሥላሴ ይህን ለማመጣጠን ከአምስቱ ዓመታት ስደት እንደተመለሱ አየር ኃይል እንዲመሰረት አድርገዋል። ምክንያቱም ጣሊያን የበላይነቱን የወሰደው በምድር ጦር ሳይሆን የተከለከለ ኬሚካል ጭምር በተጠቀመበት የአየር ውጊያ መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነበርና።

ሠራዊቱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና እንዲያገኝ የተለያዩ ሥራዎች የተሠሩትም በዚሁ ዘመን ነበር። እንደ ሐረር የጦር አካዳሚ ያሉ ዝነኛ የእጩ መኮንኖች ማሰልጠኛዎች የተገነቡት በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መንግሥት ነው። ጎን ለጎንም እንደ እንግሊዙ ሳንድረስት ባሉ ዝነኛ የጦር አካዳሚዎች የሰለጠኑ የጦር መኮንኖችም በዚሁ ዘመን የተገኙ ናቸው። የአየር ኃይሉ አባላትም እንደ አሜሪካ እና እንግሊዝ ባሉ ታላላቅ የጦር አካደሚዎች ሥልጠና አግኝተዋል። ከአባቶቻቸው ኢትዮጵያዊ ወኔን የሚወርሱት ኢትዮጵያውያን ወታደሮች በውጊያ ሜዳ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ከሚያገኙት ሥልጠና የላቀ ብቃት ማሳየት ልማዳቸው ሆኖ ቆይቷል።

ደርግ ወደ ሥልጣን በመጣባቸው የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ከመስመራዊ መኮንኖች በላይ ያሉትን የሠራዊቱን አመራሮች የማገት እና የማግለል ሙከራዎች ተደርጓል። በኋላ ላይ ግን ሠራዊቱ እንዲጠናከር የተለያዩ የማሰልጠኛ ተቋማት እንዲገነቡ ሆነ። አየር ኃይሉም የተሻለ ነጻነት ያለው እና ከዚያው በወጡ መኮንኖች የሚታዘዝ ነበረ።

ሀገር ባልተረጋጋችበት በዚያ የለውጥ ወቅት በዚያድ ባሬ የምትመራው እና የታላቋ ሶማሊያን ቅዠት ያነገበችው ሶማሊያ ኢትዮጵያን ወርራ በምሥራቅ እስከ 700 ኪሎ ሜትር፣ በደቡብ ደግሞ እስከ 300 ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያን መሬት ይዛለች። የሶማሊያ ወረራ ወቅት የነበረው የወታደር ቁጥር በጣም አናሳ ስለነበር በአጭር ጊዜ ምልመላ የገቡ ወታደሮች በኢትዮጵያዊ ወኔ ዳግም ሀገርን ከወራሪ አድነዋል። በተለይም አየር ኃይሉ ከሶማሊያ ጋር ሊነጻጸር በማይችል የተዋጊ ጄቶች ዓይነቶች እና ቁጥር የአየር ላይ ውጊያውን የበላይነት ይዞ ለድሉ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህም የሆነው በጀግንነትም ሆነ በሙያቸው የላቀ ደረጃ ላይ በደረሱት የአየር ላይ ተዋጊዎች ብቃት ነው።  

ከሶማሊያ ወረራ በኋላ በሰሜን ጦርነት የተጠመደው ደርግ ከጦርነቱ ጎን ለጎን የሠራዊቱን አቅም ሊያሳድጉ የሚችሉ በርካታ ተቋማትን ገንብቷል። ሠራዊቱም በትጥቅም በአቅምም የተሻለ አቅም እንዲኖረው ሙከራ ተደርጓል።

ኢሕአዴግ ደርግን አስወግዶ ሥልጣን ሲይዝ የቀድሞውን ሠራዊት በመበተን አዲስ የመከላከያ ሠራዊት አደረጃጀት ፈጥሯል። በዚህ አደረጃጀት ውስጥ የባሕር ኃይሉ ሙሉ በሙሉ የፈረሰ ሲሆን፣ አየር ኃይሉም ቢሆን ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ጠላት የላትም በሚል አስተሳሰብ አያስፈልግም የሚል ሀሳብ ተነስቶ ብዙ ካከራከረ በኋላ እንዲቀጥል ተደርጓል። የአየር ኃይሉ አስፈላጊነት ግን ብዙም ሳይቆይ በኤርትራ ጦርነት ተገልጧል። ከአየር ኃይሉ ተሸኝተው የነበሩት አብራሪዎች ከሰባት ዓመታት በኋላ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ የተደረገው በዚያ ጦርነት ሲሆን፣ ይህ የቀድሞ ተዋጊዎችን መመለስም የአየር ኃይሉን መዳከም የሚያሳይ ነበር።

ኢሕአዴግ ዘመን የነበረው ሠራዊት ከህገ መንግሥቱ በተቃረነ መልኩ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዘብ እንደሆነ ይነገር ነበረ። የሠራዊቱ መተዳደሪያ የሆነው “ቀዩ መጽሐፍም” ይህን ጉዳይ ነው አጽንኦት የሚሰጠው። በሌላ በኩል ሠራዊቱ ውስጥ በተለይም አመራሩ አካባቢ ወደ ጎጥ የመሳብ ምልክት መታየት ጀምሮ ነበር። ነገር ግን የሠራዊቱ አመራሮች በተቻለ መጠን ሠራዊቱ ህገ መንግሥታዊ መርሆውን እንዲከተል ለማድረግ ጥረት አድርገዋል።  

  1. ኢትዮጵያን የሚመጥን ሠራዊት የተገነባበት የሠራዊቱ ሪፎርም

የ2010 ዓ.ም ለውጥ ሲመጣ ሪፎርም ያስፈልጋቸዋል ተብለው ከተያዙት ዘርፎች መካከል የፀጥታ ዘርፉ አንዱ ነበር። ሪፎርሙ መከላከያ ሠራዊት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ የሆነ፣ ሀገር ችግር ውስጥ በገባችበት በማንኛውም ወቅት ዝግጁ የሆነ፣ በመለዮው እና በዩኒፎርሙ የሚከበር እንዲሆን አድርጎታል። ኢትዮጵያ ያለችበት ውስጣዊ እና ውጫዊ ሁኔታ ልዩ ዝግጅት እንደሚያስፈልገው የተረዳው የለውጡ አመራር ሠራዊቱን በቴክኖሎጂም በሥነ-ልቦናም የማዘጋጀት ሥራውን በትኩረት ሠርቷል።

ተዳክሞ የነበረው አየር ኃይል እንዲጠናከርና ዘመናዊ መሣሪዎችን እንዲታጠቅ ተደርጓል። ሠራዊቱ በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛ በጦርነት ጊዜ ደግሞ ባነሰ መስዋዕትነት የላቀ ድል እንዲያስመዘግብ ተደርጎ እየተዘጋጀ ነው።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ቀጣና ያላትን ስትራቴጂያዊ ቦታ እና የቀጣናውን ተለዋዋጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ባሕር ኃይል ደግሞ እንዲቋቋም ተደርጓል። ሠራዊቱ የሕገ መንግሥቱ ዘብ እና የኢትዮጵያ የመጨረሻ ምሽግ እንዲሆን ተደርጎ አየተገነባ ነው።

ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አሁን የደረሰበት የሀገርን ክብር እና ሉዓላዊነት የማስጠበቅ አቅሙ አጅግ የላቀ እየሆነ ነው።

ሠራዊቱ አሁን የብሔር እና የጎሳ አጥር ሳይገድበው በኢትዮጵያዊ መንፈስ ሀገሩን እያገለገለ ይገኛል። የኢትዮጵያን ልዕልና እውን ለማድረግ ጨለማን በጣጥሶ ለህዝቦች ብርሃንን ለመለገስ ውድ ህይወቱን እየከፈለ ይገኛል። ኢትዮጵያን የሚዞሩት ታሪካዊ ባላንጣዎቿም ይህን ክንደ ነበልባል ስለሚያውቁ ነው የሚመኙትንና የሚፎክሩትን የማይተገብሩት።

"ሕዝብ ነው ኃያል ክንዳችን ------ ሰላም ልማት ነው ቋንቋችን፣

የመፈቃቀድ አንድነት-------- እኩልነት ነው ዜማችን፣

የማንጨበጥ ነበልባል ----------እሳት ነን ለጠላታችን፣

ፍሙ ከርቀት ይፋጃል ---------- ብረት ያቀልጣል ክንዳችን።" የሚለውን የሠራዊቱን መዝሙር ያስታውሷል።

የሕዝቦችን የመኖር ዋስትና በደም እና አጥንቱ የሚያረጋግጥ እውነተኛ የህዝብ ልጅ ነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት። ይህ ሠራዊት የሰላም ዘብ ነው። ለዚህም ነው ከሀገሩ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት እና በተለያዩ ችግር ውስጥ ለገቡት የአፍሪካ ሀገራት አለኝታነቱን ያረጋገጠው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ግዳጆች ሁሉ ሕዝባዊነቱን እና ጀግንነቱን በተግባር ያረጋገጠ ሠራዊት ነው። ትላንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ ይሄው ሰራዊት ጀግንነቱን ጠብቆ ኢትዮጵያን በደሙ እያጸና የመጣ አሁንም ይህንኑ በላቀ ግዳጅ አፈጻጸሙ እያስመሰከረ ቀጥሏል።

በለሚ ታደሰ


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top