በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት አገልግሎት አሰጣጥ በተጨባጭ የህዝቡን እንግልት እየቀረፈ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ እንዲሁም በሰሜን ሸዋ ዞን ልዩ ልዩ ወረዳዎች የተዘረገው የቀበሌ አደረጃጀት እየሰጠ ያለውን የህዝብ አገልግሎት ተዘዋውረው የጎበኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፤ "የህዝባችንን ለውጥ ለማየት ከሰራን ሁሉም ነገር ይሳካል" ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡም አገልግሎቱን ለመጠቀም እያደረገ ያለው ንቁ ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡
የቀበሌ አደረጃጀት አገልግሎት ተግባራዊ እንዲሆን 50ሺህ አመራሮች በቀበሌ ደረጃ ተመድበው ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በቀበሌ የተጀመረው አዲሱ የአገልግሎት አሰጣጥ በዘላቂነት ተግባራዊ በማድረግ የላቀ ውጤት እንዲመጣ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደረጋልም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
በምስራቅ ሸዋ ዞን 302 ቀበሌዎች በአዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት የተዋቀሩ ሲሆን 281 የሚሆኑት ወደ ስራ መግባታቸውን የዞኑ አስተዳደሪ አቶ አባቦ ማሞ ለኢቲቪ ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል አዲስ የተጀመረው የቀበሌ አደረጃጀት ቀድሞ የነበረውን እንግልት፣ የገንዘብ፣ የግዜና ጉልበት ብክነት ያስቀረ ነው ሲሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ ነዋሪዎች ለኢቲቭ ገልፀዋል፡፡
የተዘረገው የቀበሌ አደረጃጀት እንግልታቸውን ያስቀረላቸው መሆኑን የሚናገሩት የሉሜ ወረዳ ጠዴ ድልድማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ግርማ ወልዴ፤ በአዲሱ አደረጃጀት ምክንያት የሚፈልጉትን አገልግሎት ከመኖሪያ ቀያቸው በቅርበት አግኝተው በመገልገላቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመሀመድ ፊጣሞ