ቢትኮይን ለመጀመሪያ ጊዜ 100 ሺህ ዶላር መመንዘር ጀመረ

8 Days Ago 150
ቢትኮይን ለመጀመሪያ ጊዜ 100 ሺህ ዶላር መመንዘር ጀመረ

ቢትኮይንን የተሰኘው የዲጂታል መገበያያ ገንዘብ (ክሪፕቶ ከረንሲ) በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል።

በዚህም የአንድ ቢትኮይን ዋጋ በ100 ሺህ ዶላር በመመንዘር ላይ ሲሆን ይህም በዲጂታል መገበያያ ገንዘቡ ታሪክ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

የቢትኮይን ዋጋ እንዲህ ሊጨምር የቻለው ተመራጩ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የክሪፕቶ ከረንሲን የሚደግፉ ፖሊሲዎችን እንደሚቀበሉ በማሳወቃቸው መሆኑ ተገልጿል።

ትራምፕ የቀድሞን የአሜሪካ የሴኪውሪቲስ እና ኤክስቼንጅ ኮሚሽነር ፖል አትኪንስ የሃገሪቱ የስቶክ ገበያ የሆነውን ዎል ስትሪት እንዲመሩ ማጨታቸው ከተሰማ ከሰዓታት በኋላ የቢትኮይን ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት መሆኑም ተነግሯል፡፡

ሚስተር አትኪንስ አሁን ካሉት የሴኪውሪቲስ እና ኤክስቼንጅ ኮሚሽን ኃላፊ ጋሪ ጌንስለር የበለጠ የክሪፕቶ ከረንሲ ደጋፊ ስለመሆናቸውም ነው የተገለፀው።

ዶናልድ ትራምፕ ምንም እንኳን ከዚህ በፊት ክሪፕቶከረንሲን የተቹ ቢሆንም አሁን ግን አሜሪካን የምድራችን የክሪፕቶከረንሲ መዲና አደርጋታለሁ ሲሉ ቃል መግባታቸውን ተከትሎ የቢትኮይን ዋጋ እየናረ መምጣቱ ተጠቁሟል።

በተለይም ባለፈው ወር ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ካሸነፉ በኋላ የቢትኮይን ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ሲያሳይ መቆየቱ ነው የተገለፀው።

አንዳንድ ትልልቅ ኩባንያዎችና ተቋማት ቢትኮይንን እንደ ገንዘብ መቀበል መጀመራቸውም ለተፈላጊነቱ ማደግ ሌላ ምክንያት ነው ተብሏል።

የዲጂታል መገበያያ ገንዘቡ 100 ሺህ ዶላር መግባቱን ተከትሎ በዓለም ዙሪያ ያሉ የቢትኮይን ተጠቃሚዎች እና ደንበኞች ደስታቸውን እየገለፁ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ ነው።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top