የ11 ዓመት ሕፃን ልጅ በማገት 4 ሚሊዮን ብር የጠየቀው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ

14 Hrs Ago 64
የ11 ዓመት ሕፃን ልጅ በማገት 4 ሚሊዮን ብር የጠየቀው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ለሚ ከተማ የ11 ዓመት ሕፃን ልጅ በማገት ወደ ሸገር ከተማ በማምጣት 4 ሚሊዮን ብር የጠየቀውን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር አውሏል።

አበራ አላዩ  የተባለው ግለሰብ ከሚኖርበት ሸገር ከተማ በመነሳት አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ዎኮ ፍቅረሰላም ቀበሌ ከሚኖር ገብረመድህን አላዩ ከተባለ ወንድሙ ጋር በመሆን ህዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 4:30 እገታውን መፈፀማቸውን ፖሊስ ገልጿል፡፡

ድርጊቱንም በወረዳው ለሚ ከተማ የሚገኘውን አውሌ ገብሩ የተባሉ ግለሰብ መኖሪያ ቤትን ሰብረው በመግባት ጥይት ተኩሰው በማስፈራራት የታጋቹን እናትና እህቶቹን እጅ በገመድ በማሰር ሕፃን ባሳዝነው አውሌን አግተው መውሰዳቸው ተጠቅሷል፡፡

አጋቾቹ ሕፃኑን ለሦስት ቀናት ዋሻ ውስጥ በማሳደር በእግር እስከ ፍቼ ከተጓዙ በኋላ ሁለተኛው አጋች ገብረመድን አላዩ ወደ አማራ ክልል መመለሱም ነው የተገለፀው፡፡

ከዚያም አጋቹ ሕፃኑን ህመምተኛ በማስመሰል በብርድልብስ በመሸፈን በሕዝብ ትራንስፖርት ከፍቼ ከተማ ወደ ሸገር ከተማ ቡራዩ ክ/ከተማ በማድረስ በተከራየው መኖሪያ ቤት ውስጥ በመደበቅ ለሕፃኑ አባት ስልክ በመደወል 4 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል መጠየቁ ተጠቅሷል።

ይህ ካልሆነ ግን ሕፃኑን በሕይወት እንደማያገኘው በማስፈራራት ላይ እንዳለ ጉዳዩን የሰማው አዲስ አበባ ከተማ የሚኖረው የሕፃኑ አጎት ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃውን ማድረሱም ተገልጿል፡፡

በዚህም ፖሊስ መረጃውን መነሻ በማድረግ ተጠርጣሪውን ተከታትሎ በተከራየው መኖሪያ ቤት ውስጥ ከተባባሪ ባለቤቱ ጋር እጅ ከፍንጅ በመያዝ በቁጥጥር ስር አውሎ የሕፃኑን ሕይወት መታደግ መቻሉን የፖሊስ መረጃ አመልክቷል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top