በምዕራባውያን ምክንያት የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ወደ አለም አቀፋዊ ግጭት እየተቀየረ ነው - ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቱን

21 Days Ago 425
በምዕራባውያን ምክንያት የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ወደ አለም አቀፋዊ ግጭት እየተቀየረ ነው - ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቱን

ዩክሬን የምዕራባውያንን ከባድ የጦር መሣሪያዎች ተጠቅማ ሩሲያን እንድትመታ ምዕራባውያኑ ከፈቀዱ በኋላ የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ወደ ዓለም አቀፋዊ ግጭት እያመራ ነው ሲሉ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናገሩ።

ፑቲን አክለውም የዩክሬን ጥቃት ከቀጠለ ሞስኮ መልሷ አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ለምዕራባውያን አስጠንቅቀዋል።

ለዚህም ማሳያ ሩሲያ ዩክሬን ለተጠቀመቻቸው አሜሪካ እና እንግሊዝ ሰራሽ ሚሳኤሎች ግብረ መልስ እንዲሆን አዲስ አይነት ሃይፐርሶኒክ መካከለኛ ርቀት ባለስቲክ ሚሳኤል በዩክሬን ወታደራዊ ተቋም ላይ በመተኮስ ምላሽ ሰጥታለችም ብለዋል።

ይህ የመጨረሻው አይደለም ያሉት ፑቲን፤ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ተጨማሪ ጥቃቶች ሊከተሉ ይችላሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ነገር ግን ሩሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅማዋለች የተባለውን አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ከዚህ በሃላ ከተጠቀመች አስቀድማ ለሲቪሎች ማስጠንቀቂያ እንደምትሰጥ ነው ፑቲን የተናገሩት።

ዩክሬን የአሜሪካ ሚሳኤሎችን በሩሲያ ላይ እንድትጠቀም በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ፍቃድ ከተሰጣት በኋላ ዩክሬን በስድስት አሜሪካ ሰራሽ እና በእንግሊዝ ሰራሽ ሚሳኤሎች ሩሲያን መምታቷን ፕሬዝዳንት ፑቲን አስታውሰዋል።

ይህንን ተከትሎ ፑቲን በሰጡት መግለጫ፤ "ከዛ ቅጽበት ጀምሮ፣ ደጋግመን እንዳስረዳነው፣ ቀደም ሲል በምዕራቡ ዓለም የተቀሰቀሰው የዩክሬን እና ሩሲያ ግጭት ዓለም አቀፋዊ ባህሪ እየኖረው ነው" ብለዋል ሲል የዘገበው ሮይተርስ ነው።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በበኩላቸው፤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የባሊስቲክ ሚሳኤል መጠቀሟ ለሰላም ምንም ፍላጎት እንደሌላት ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ጥቃቱ የሩስያ መሪ ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን ለማባባስ የወሰዱት "ሁለተኛ እርምጃ" ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ሩሲያ ከቻይና፣ ብራዚል፣ የአውሮፓ ሀገራት እና አሜሪካ የሚደረጉ የሰላም ጥሪዎችን ችላ በማለት ከአንድ ሺህ ቀናት በፊት የጀመረችውን ጦርነት ለማራዘም ሁሉንም ነገር እያደረገች ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ አክለውም "አለም ጠንካራ ምላሽ መስጠት አለበት ሩሲያ በኃይልም ቢሆን ወደ እውነተኛ ሰላም እንድትገባ ማስገደድ አለባት። ይህ ካልሆነ ግን ማለቂያ የለሽ ጥቃቶች፣ ዛቻዎች እና አለመረጋጋቶ ይኖራሉ፤ ይህ ደግሞ በዩክሬን ላይ ብቻ አይደለም ለአለምም አስጊ ነው" ብለዋል።

በናርዶስ አዳነ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top