ከ40 ዓመታት በኋላ ሰቆቃን ማስታወስ ወይስ ልማትን መደገፍ?

14 Hrs Ago 406
ከ40 ዓመታት በኋላ ሰቆቃን ማስታወስ ወይስ ልማትን መደገፍ?

ቻይናዊው ፈላስፋ ላኦ ዙ "ለሰው ዓሣ ከሰጠኸው ለአንድ ቀን ትመግበዋለህ፤ ሰውን ዓሣ እንዲያጠምድ ካስተማርከው ግን ዕድሜ ልኩን ትመግበዋለህ" ይላል። ይህን መነሻ በማድረግም "Don't give a fish, but teach how to fish" (ለሰው ዓሣን አትስጥ፣ ዓሣን ማጥመድን አስተምረው) የሚል አባባል ይነገራል። 

ሥልጣኔዋን ዘርፈው፣ የቀረውን ቀብረው አፍሪካን በቅኝ ግዛት የተቀራመቱት ምዕራባውያን አፍሪካን ዓሣን እንዴት እንደምታጠምድ አያስተምሯትም። ይልቁንስ ዓሣን በጥቂት በጥቂቱ እየሰጡ ጠባቂ ሲያደርጓት ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ምክንያቱ ደግሞ አፍሪካ ዓሣን ማጥመድ ከጀመረች የሀብታቸው ምንጭ እንደሚደርቅ በማሰባቸው ነው። 

የአፍሪካን ረሃብ በመገናኛ ብዙኃኖቻቸው እያራገቡ የተቀቀለ ስንዴ የሚልኩላት ለዚህ ነው። ለዚህም ነው ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም እንደሚሉት በረድኤት ድርጅቶቻቸው በኩል የሚያቀርቡትን ከ85 በመቶ በላይ ገንዘብ መልሰው ለስለላ የሚጠቀሙበት። ለዚህ ደግሞ ተባባሪዎቻቸው ሀገራቱን የሚመሩት ቡድኖች እና ለዚሁ የሚመድቧቸው የረድኤት ሠራተኞቻቸው ናቸው። 

አፍሪካ ውስጥ በምግብ ራስን ስለመቻል ያነሳ መሪ አመጽ ተቀስቅሶበት ዕረፍት እንዲያጣ ይደረጋል። እምቢ ብሎ እርምጃውን ከቀጠለ ደግሞ ይወገዳል። ለዚህም የቡርኪና ፋሶ ፕሬዚዳንት የነበረው ቶማስ ሳንካራን በያዘው ጠንካራ አቋም ሀገሩን መለወጥ በመጀመሩ ያስወገዱበት መንገድ ማሳያ ነው። ከዚያ ያለፈውን ደግሞ በሰብዓዊ መብት ረገጣ ስም የክስ መዓት ያዘንቡበታል፤ መፈንቅለ መንግሥት ያስደርጉበታል። 

መገናኛ ብዙኃኖቻቸው እና የኪነ-ጥበብ ሰዎቻቸውም ይህንኑ መንገድ የሚከተሉ ናቸው። እዚህ ጋር አንድ ጉዳይ ማንሳቱ አስፈላጊ ነው። በአውሮፓውያኑ 1984 በኢትዮጵያ ውስጥ የከፋ ረሃብ ነበር። በዚያን ወቅት በአጋጣሚ ከቢቢሲ ሬዲዮ ስለ ረሃቡ የሰማው አየርላንዳዊው ቦብ ጌልዶፍ የሙዚቃ ቡድን ሰብስቦ “Do they know it is Christmas?” (ለመሆኑ ገና መሆኑን ያውቃሉ?) በሚል ርዕስ አንድ ነጠላ ዜማ አወጣ። ያ ዜማም በእንግሊዝ ውስጥ ለአምስት ሳምንታት የሽያጭ ሰንጠረዡን ተቆጣጥሮ ቆይቷል። ከዚያ በተገኘው በሚሊዮን የሚቆጠር ፓውንድም ጊዜያዊውን ረሃብ ለማስታገስ ተችሏል። ይህ ሰው ለሰው በተለይም የኪነ-ጥበብ ሰው ለሰው ልጅ የሚያደርገው ዋጋም ሙገሳም የማይጠየቅበት በጎ ተግባር ነው።

ሙዚቃው የቦብ ጌልዶፍን 80ኛ ዓመት እና ሙዚቃው የተሠራበትን 40ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ ታትሟል። ከዚህ በፊት በአውሮፓውያኑ 1989  "Band Aid II"፣ በ2004 "Band Aid 20"፣ በ2014 "Band Aid II 30" በማለት ሙዚቃው እየታተመ ተሰራጭቷል። ይህም አንዳንድ የሙዚቃ ቡድኑ አባላትን ጨምሮ በተለያዩ ሰዎች ትችት ገጥሞታል። የትችቱ መነሻ ደግሞ ከ80 ዓመታት በኋላ "አፍሪካ ዛሬም ምስኪን ናት፤ ሁሌም ከችግሯ የሚያወጧት ምዕራባውን ናቸው" የሚል አደምታ ስላለው ነው። ከተቺዎቹ አንዱ የአፍሪካ የግጭት አፈታት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሆነው የሠሩት የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር አዴኬዬ አዴባጆ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ሙዚቃውን ከአስርት ዓመታት በኋላ ዛሬም እንደ አዲስ ማሳተም ያስፈለገው አፍሪካን አቅመ ቢስ እንደሆነች እና መዳኛዋም የነጮች እርዳታ ብቻ እንደሆነ ለማሳየት ነው። ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃኖቻቸው የአፍሪካን ደካማነት ለማሳየት አበክረው እንደሚሠሩ ነው አዴባዮ የሚገልጹት። 

ዘ ታይምስ ጋዜጣ እንዳስነበበው ደግሞ የዚህ ሙዚቃ ዳግም መለቀቅ በሙዚቃ ስራው የተሳተፉትንም ጭምር ያስቆጣ ድርጊት ሆኗል። በአውሮፓውያኑ 2014 ሙዚቃው ዳግም ተሰርቶ ሲለቀቅ በሙዚቃ ስራው ከተሳተፉ አርቲስቶች መካከል እንግሊዛዊው ኢድ ሺራን የሙዚቃን ዳግም መለቀቅ ተቃውሟል።

ኢድ ሺራን አሁን ላይ ሙዚቃው የአፍሪካን ወቅታዊ ሁኔታ እንደማይገልጽ በሰነዘረው ወቀሳው፥ በአውሮፓውያኑ 2014 በተለቀቀው ሙዚቃ ላይ መሳተፉ ተገቢ አለመሆኑን ጨምሮ ስለመግለጹ ነው ጋዜጣው ያስነበበው።

ከ40 ዓመትታ በፊት ሰብዓዊነትን በማስቀደም እንዲህ ያለውን ሙዚቃ ሰርቶ ለተቸገሩ መድረስ ተገቢ ነበር የሚለው ፉሴ ኦዲጄ ደግሞ፤ አሁን ግን ሙዚቃውን ዳግም መስራቱ ፈፁም ተገቢ አይደለም በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል።

ፉሴ ኦዲጄ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ሙዚቃው የተጠቀማቸው የግጥም ስንኞች አፍሪካን በመጥፎ የሚስሉ በመሆናቸው ዳግም መለቀቁ ተገቢ አለመሆኑን ገለጿል።

በአንድ ወቅት ችግር ገጥሞን ነበር የሚለው ፉሴ ኦዲጄ፤ ሙዚቃው የተሰራው አፍሪካን በሚጠቅም እና ያንን ችግር እንዴት እንዳለፍነው በሚገልፅ መልኩ ቢሆን ኖሮ ተገቢ ይሆን ነበር ሲል ነው የገለጸው።

ችግሮች ሲፈጠሩ የመፍትሄው አካል መሆን ከሁሉም ቢጠበቅም፤ ሁሌም መፍትሄው ከውጭ የሚመጣ ማስመሰል ለአህጉሪቱ ሌላ ከባድ የማንነት ቀውስ የሚፈጥር ነው ሲል አስረድቷል።

እነ ቦብ ጌልዶፍ በ2014 በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ላጋጠመው የኢቦላ ወረርሽኝ መፍትሄ ለማምጣት ሲንቀሳቀሱ በወቅቱ ችግሩን ስላጠፋው አፍሪካዊ ዶክተር ምንም አለማለታቸውን ፉሴ ኦዲጄ አስታውሷል።

ይህ አካሄድ አፍሪካ የርሃብ፣ የችግር እና የመጥፎ ነገሮች ሁሉ መናኸሪያ፣ ህዝቧም ችግሮች ሲገጥሙት በራሱ መፍትሄ ማበጀት የማይችል ጥገኛ ሆነው እንዲታዩ የሚያደርግ፤ የአፍሪካ ታዳጊዎች ጥሩ የማንነት መሰረት ይዘው እንዲያድጉ የማይረዳ በመሆኑ ሙዚቃው በድጋሚ መታተሙ ተገቢ አለመሆኑን ገለጿል።

ኢትዮጵያ ግን ዓሣውን ለማጥመድ እየሠራች ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአውሮፓውያን አቻዎቻቸው ጋር ስለ አፍሪካ ስደተኞች ሲወያዩ የሚያነሱት አንዱ ነጥብ የስደቱ ምክንያት አውሮፓውያኑ አፍሪካ ውስጥ የሠሩት ሥራ መሆኑን ማስረዳት ነው። አውሮፓውያን የአፍሪካን ሀብት ከመቀራመታቸውም በላይ ዛሬም በእጅ አዙር አፍሪካን እየጠመዘዙ መሆኑን የሚጠቅሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መፍትሔውም ራሳቸው አውሮፓውያኑ ጋር እንደሆነ ይገልጻሉ። ይኸውም የዕለት እርዳታ በመስጠት ጥገኝነትን እና ጠባቂነትን ከማበረታታት ይልቅ አፍሪካ በዘላቂነት ራሷን እንድትችል ማድረግ እንደሆነ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚያስረግጡት። 

ስንዴን በማምረት ብቻ ከስንዴ ለማኝነት መውጣት እንሚቻል የሚያውቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ወደ አመራር እንደመጡ በትኩረት ከሠሩባቸው መስኮች አንዱ ግብርና ነው። ግብርናው ላይ የተሠራው ሪፎርም ለውጥ ማምጣት ከጀመረ ውሎ አድሯል። የተበጣጠሱ ማሳዎች በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ምርታማነታቸው ጨምሯል፤ በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ ለማምረት ተችሏል፤ በታሪክ ስንዴ አምርተው የማያውቁት የአፋር፣ የቦረና እና የሀረርጌ ሰፋፊ መሬቶች ስንዴ በኮምባይነር የሚሰበሰብባቸው ሆነዋል። ይህም ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ መግዛትን ከማቆም አልፋ ወደ ውጭ የምትልክበት ደረጃ እንድትደርስ አድርጓታል። የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እና ተቋማትም ይህንኑ ተጨባጭ እውነታ መስክረዋል።

‘ወርልድ ግሬይን’ የተሰኘው ድረ-ገጽ "የስንዴ አብዮት" በሚል በሠራው ዘገባ ኢትዮጵያ የውሃ እጥረትን የሚቋቋሙ የስንዴ ዝርያዎችን በመጠቀም፣ የመስኖ እርሻዎችን በማስፋፋት ስንዴን በከፍተኛ ደረጃ እያመረተች እንደሆ አትቷል። የአፍሪካ ልማት ባንክም ኢትዮጵያ ስንዴ የማምረት አቅምን በሄክታር ከ2 ወደ 4 ቶን በማሳደግ ረገድ ያስመዘገበችውን ስኬት አድንቆ፣ በሀገሪቱ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ እና የኢኮኖሚ ሽግግሩ እንዲሳለጥ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። 

እንደ ዓለም አቀፉ የበቆሎ እና የስንዴ ማሻሻያ ማዕከል (CIMMYT) ያሉ ተቋማት ኢትዮጵያ በሰብል ምርት እያመጣችው ያለችውን ለውጥ አድንቀዋል። ‘ኪሊሞ ክዋንዛ’ የተሰኘው እና በአፍሪካ ግብርና እና የምግብ ዋስትና ላይ ጥናቶችን የሚያወጣው ተቋም፥ ኢትዮጵያ ግብርናን ለማዘመን የሰጠችው ትኩረት እንዲሁም የግብርና ቴክኖሎጂዎች እና የግብርና ግብዓቶችን ከቀረጥ ነጻ ማድረጓ ውጤታማ እንዳደረጋት ያትታል። ይህም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሊማሩበት የሚገባ ልምድ እንደሆነ ነው ተቋሙ የሚገልፀው። 

‘ወርልድ ግሬይን’፥ ኢትዮጵያ ከሀገራዊ ፍላጎቷ በ32 ሚሊዮን ኩንታል የበለጠ ስንዴ ማምረቷ ታሪካዊ ስኬት እንደሆነ ዘግቧል። ይህ ስኬት ኢትዮጵያ ድርቅን የሚቋቋም የስንዴ የእሴት ሰንሰለት በመፍጠር ቀጣናዊ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና ለመጫወት የያዘችውን ዕቅድ እንደምታሳካ ማረጋገጫ እንደሆነም ነው የጠቀሰው።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ግብርናን ተግብራ በስንዴ ምርት ያመጣችው ስኬት በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚቻል ማሳያ እንደሆነ መገናኛ ብዙኃኑ አመላክተዋል። ሀገሪቱ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ሜካናይዜሽን እና ፈጠራ ላይ ያተኮረ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ካገኘች ውጤታማነቱ የተረጋገጠ የግብርና አመራሯን በማሳደግ ዓላማዋን ልታሳካ እንደምትችል ነው የሚያትቱት።

በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ስኬት ሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ ያካሄደችው ሰፊ ሪፎርም እንዲሁም ዘርፉን የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማሻገሪያ ለማድረግ የተለመችው ትልም ውጤት ነው ይላሉ ዘገባዎቹ።

በሴፕቴምበር 2023 የወጣው የብሉምበርግ ዘገባ የኢትዮጵያ መንግሥት የስንዴ ምርትን በ27 በመቶ በማሳደግ ትርፍ አምርቶ ወደ ውጭ ለመላክ አቅዶ እየሠራ እንደሆነ ይጠቁማል። ሀገሪቱ በአሁኑ ሰዓት ይህን አሳክታ ስንዴን ከውጭ መግዛትን ከማቆም አልፋ ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች።  

‘ወርልድ ግሬይን’ ደግሞ ኢትዮጵያ 500 ሺህ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮችን በመደገፍ እና ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን በማለማመድ በስንዴ ምርት የመጣውን ውጤት ለማስቀጠል በሜይ 2024 የ94 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ማድረጓን ጠቅሷል። ይህ መርሐ ግብር በቤተሰብ ደረጃ ያለውን ገቢ በማሳደግ 2.3 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ በዚሁ ዘገባ ተጠቅሷል። 

ዓለም አቀፉ የበቆሎ እና የስንዴ ማሻሻያ ማዕከል (CIMMYT) በበኩሉ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ያመጣችው ለውጥ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት እንደሆነ ይጠቅሳል። እነዚህ የተቀናጁ ጥረቶች ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን በመቀየር፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ለቀጣናው እንዲሁም ለዓለም አቀፍ የስንዴ ገበያ የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያጎሉ እንደሆኑ ነው ዘገባዎቹ የሚያመላክቱት።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top